የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ9 ቢሊዮን በላይ ዶላር ገቢ ማግኘቱን ገለጸ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በ2025/2026 በጀት ዓመት የዓለም አቀፍ ፈተናዎችንና የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን በመቋቋም 9.1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ገልጿል።

አየር መንገዱ በዓመቱ 20.7 ሚሊዮን ደንበኞችን በማጓጓዝ የ10 በመቶ እድገት ያሳየ ሲሆን፣ የጭነት አቪየሽን አገልግሎቱም ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ16 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

​የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በሰጡት መግለጫ፣ በበጀት ዓመቱ አራት አዳዲስ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን በመጨመር አጠቃላይ የመዳረሻዎችን ቁጥር 150 ማድረሱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የሀገር ውስጥ መዳረሻዎችን ከ22 ወደ 25 ከፍ በማድረግ የአየር መንገዱን ተደራሽነት ማስፋፋት ተችሏልም ብለዋል።

የበረራ አቅምን ለማጠናከርም ዘጠኝ አዳዲስ አውሮፕላኖች በግዢና በኪራይ ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን፣ ለኢትዮጵያ አቪየሽን ዩኒቨርሲቲ ስልጠና የሚውሉ ስምንት DA40NG አውሮፕላኖች ተገዝተዋል።

​ምንም እንኳ አየር መንገዱ ጠንካራ የእድገት መስመር ላይ ቢሆንም፣ የተቀመጡ አጠቃላይ ዕቅዶችን ሙሉ በሙሉ እንዳያሳካ የውጭ ተፅዕኖዎች እንቅፋት ሆነዋል ተብሏል።

በገልፍ ሀገራት በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ወደ ቀጠናው የሚደረጉ 10 ያህል በረራዎች መቋረጣቸው፣ የትላልቅ አውሮፕላኖች እጥረት፣ እንዲሁም አሜሪካና አንዳንድ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የጣሏቸው የጉዞ ማዕቀፎች የገቢ አቅሙን ገድበውታል።

​በተጨማሪም በጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች ሳቢያ የነዳጅ ዋጋ በመናሩ የአየር መንገዱ የወጪ መጠን ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ25 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተገልጿል።

በመካከለኛው ምስራቅ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት “በአዲስ አበባ የነዳጅ እጥረት አውሮፕላኖቻችንን በጎረቤት ሀገራት በመላክ ከፍተኛ ወጪ እንድናወጣ አድርጎናል” ሲሉም ዋና ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።

ሆኖም ግን አየር መንገዱ ያስቀመጠውን ሙሉ እቅድ እንዳያካሂድ በርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ተጽዕኖዎች እንዳጋጠሙት ስራ አስፈጻሚው አልሸሸጉም።

ለዚህም የቀጣናዊ ጦርነትና የበረራ ክልል መዘጋት የሚለው የሚገኝበት ሲሆን በተለያዩ አካባቢዎች በረራዎች በመቋረጣቸው መስመር ለመቀየር እንደተገደደ አስታውቋል።

በሌላ በኩል አሜሪካ አዳዲስ የጉዞ ማዕቀብ በመጣሏ ምክንያት በአፍሪካ እና በሰሜን አሜሪካ መካከል ያለው የጉዞ እንቅስቃሴ መቀነሱን ገልጿል።

በአፍሪካ ደግሞ በኮንጎ በተከሰተው በኢቦላ ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት በተጣሉ የጉዞ ገደቦች የመንገደኞች እንቅስቃሴ መግታቱን ጠቅሷል።

እነነዚህ ተጽዕኖዎች ቢኖሩም አየር መንገዱ ከአጠቃላይ ሥራውና ካስመዘገበው ከፍተኛ የገቢ እድገት አንጻር በዓመቱ አዎንታዊና ስኬታማ አፈጻጸም አድርጎ እንደሚያየው አስታውቋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአስመራ የሚገኘው ገንዘቡ በሁለቱ ሀገራት የፖለቲካ ልዩነት ምክንያት እስካሁን እንዳልተለቀቀለት አስታውቋል።

በተጨማሪም አየር መንገዱ በተለያዩ ሀገራት ገንዘቦቹ እንደተያዙበት ያነሱ ሲሆን፣ በርካታ ገንዘብ በሩሲያ እና ሞዛምቢክ እንደሚገኝ በመግለጽ ይህንንም ለማውጣት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *