የዲጂታል ጤና ቴክኖሎጂ ኩባንያ የሆነው “ሜድራፋ” (Medrafa) የጤና ቴክኖሎጂውን ከኢንሹራንስ ጋር በማስተሳሰር የበለጠ ውጤታማና ተደራሽ ለማድረግ “አይኪቪያ” (IQVIA) ከተሰኘ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የጤና መድን ድርጅት ጋር ወደ ስራ ለመግባት የሚያስችል ህጋዊ ስምምነት መፈራረሙን አስታወቀ፡፡
የ“ሜድራፋ” ተባባሪ መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ቢኒያም ተስፋዬ እንደተናገሩት፤ ስምምነቱ የተቀናጀ የኢንሹራንስ ስርዓት ባለመኖሩ የተፈጠረውን የጤና ኢንሹራንስ ክፍተት ለመሙላት ያስችላል፡፡
እንደ አቶ ቢኒያም ገለፃ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የደንበኞቻቸውን የካሳ ጥያቄ (Claim) ከቀረበበት ጀምሮ እስከሚጠናቀቅበት ድረስ ያለውን ሂደት በዲጂታል መንገድ ለመከታተል፣ ለማስተዳደርና ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል ስርዓት (Insurance Claim Management System) ባለመኖሩ ተቋማት የጤና ኢንሹራንስ ለማቅረብ ይቸገራሉ፡፡ የጤና ኢንሹራንስ ስራዎችን አቀናጅቶ የሚሰራ የተደራጀ የአሰራር ስርዓት ካለመኖሩ በተጨማሪ በኢንሹራንስ ስም የሚፈፀሙ የማጭበርበር ድርጊቶችም በጤና ኢንሹራንስ ተደራሽነት ላይ ተፅዕኖ ፈጥረዋል፡፡
ስምምነቱ የጤና ኢንሹራንስ ስራዎችን አቀናጅቶ የሚሰራ የተደራጀ የአሰራር ስርዓት በመፍጠር የጤና ኢንሸራንስ ለማቅረብ የሚያግዝ ትብብር ለመፍጠር ያስችላል፡፡ ውጤታማነትን በመጨመርና ግልጽነትን በማስፈን በኢንሹራንስ ስም የሚፈፀሙ የማጭበርበር ድርጊቶች እንዲቀንሱም ያደርጋል፡፡ ይህም የጤና ኢንሹራንስን ደህንነት በማረጋገጥ የጤና ተደራሽነትን ያስፋፋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የመድኃኒት ዋጋ እንዲጨምርና የህክምና ክፍያ እንዲወደድ አንዱ ምክንያት የተቀናጀ የኢንሹራንስ ስርዓት አለመኖሩ መሆኑን ጠቁመው፣ ስምምነቱ የኢንሹራንስ ጥያቄን በማሳለጥ የህክምና ዋጋ እንዲቀንስ እንደሚያደርግም አመልክተዋል፡፡
“አይኪቪያ” (IQVIA) በአሜሪካ፣ በሩቅ ምስራቅ፣ በአፍሪካና ሌሎች የዓለም አካባቢዎች የጤና መድን አገልግሎት ላይ የተሰማራ ዓለም አቀፍ ተቋም መሆኑን ጠቁመው፣ በአፍሪካ እንዲህ ዓይነት ስምምነት ሲፈራረም ይህ የመጀመሪያው መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ “አይኪቪያ” ከ“ሜድራፋ” ጋር በአጋርነት ለመስራት የወሰነውና ወደ ስራ የመግቢያ ስምምነቱን (Teaming Agreement) የተፈራረምነው የኢትዮጵያ ገበያ አዋጭ እንደሆነ አምኖበት ነው” ብለዋል፡፡
አቶ ቢኒያም እንዳሉት፤ ስምምነቱ “ሜድራፋ” የጤናውን ዘርፍ ችግሮች በቴክኖሎጂ በታገዘ አሰራር ለመፍታት የሚያደርገው ሰፊ ጥረት አካል ነው፡፡ የጤና ተቋማት አለመናበብ፣ የጤና ኢንሹራንስ አለመኖር እና የመድኃኒት ትዕዛዞች ስህተት በኢትዮጵያ ከሚታዩ የጤናው ዘርፍ ችግሮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ዲጂታል የጤና ቴክኖሎጂዎች እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡ “ሜድራፋ” ለእነዚህ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ያበጀ ዲጂታል ቴክኖሎጂ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ኩባንያው የሚሰራው በጤና መረጃዎች ልውውጥ ላይ ሲሆን፤ ከግዥ ትዕዛዝ እስከ ክፍያ ድረስ ያለውን የኢንቨንቶሪ ስርዓት በዲጂታል ስርዓት እንዲመራ ያስችላል ብለዋል፡፡
መድኃኒቶች የሚታዘዙበትንና የሚሰጡበትን ስርዓት በማዘመን የህክምና ስህተቶችን መቀነስ፣ አሰራሩን የበለጠ ውጤታማ በማድረግ የህክምና ዋጋ እንዲቀንስ ማድረግ፣ የህክምና መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ታካሚዎች የህክምና መረጃዎቻቸው ባለቤት እንዲሆኑ ማስቻል የቴክኖሎጂው ቁልፍ ዓላማዎች እንደሆኑም አስረድተዋል፡፡
ቴክኖሎጂው የመድኃኒት ትዕዛዞችን ወደ ኤሌክትሮኒክ ስርዓት በማሸጋገር ደህንነታቸው እንዲጠበቅ፣ ዋጋ እንዲቀንስ እንዲሁም ታካሚዎች የተሻለ ግንዛቤና የወሳኝነት ሚና እንዲኖራቸው የሚያስችል ነው፡፡ የጤና ተቋማትን፣ የኢንሹራንስ ድርጅቶችን፣ ክሊኒካል ሲስተሞችን ጨምሮ ዲጂታል የጤና ስርዓቶች እንዲናበቡ በማድረግ የአቀርቦት ሰንሰለቱን ያዘምናል፤ ፋርማሲዎች ብክነት እንዲቀንሱ፣ ጊዜ ያለፈባቸውን መድኃኒቶች እንዲያስወግዱ እና የመድኃኒት ፍላጎትን እንዲተነብዩ ያደርጋል፡፡ በኢትዮጵያ 58 በመቶ የሚሆነው የመድኃኒት ትዕዛዝ ስህተት እንዳለበት ጠቁመው፤ “ሜድራፋ” ይህን የትዕዛዝ ስህተት መጠን ወደ ነጠላ አሃዝ የማውረድ እቅድ እንዳለውም አመልክተዋል፡፡
ዲጂታል የጤና ቴክኖሎጂዎች አስተማማኝና የሀገርን ችግር በዘላቂነት መፍታት የሚችሉ እንዲሆኑ ዓለም አቀፍ የጤና ደረጃዎችን የሚመጥኑ እና በሀገር ውስጥ አቅም የበለፀጉ ሊሆኑ እንደሚገባ የተናገሩት አቶ ቢኒያም፤ “ሜድራፋ” የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በሚገነዘቡ ባለሙያዎች ከመሰራቱ በተጨማሪ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸውን የጤና መረጃ ደረጃዎችን (SNOMED CT እና FHIR) እንደሚጠቀም ገልጸዋል፡፡
“ሜድራፋ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የበለፀገና የሚመራ በመሆኑ፣ ቴክኖሎጂው የጤና ስርዓቱን በራስ አቅም የማዘመንና የመምራት ጥረት አካል ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የአሰራር ስርዓትን በመጠቀም የሀገርን ችግር በሀገር በቀል ተቋምና ባለሙያ፣ ትርጉም ባለውና ዘላቂ በሆነ መንገድ የመፍታት የረጅም ጊዜ ፕሮጀክት ነው” ብለዋል፡፡
“ሜድራፋ” እስካሁን ከ200 በላይ ከሚሆኑ ፋርማሲዎች ጋር እንደሚሰራና ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ልውውጥ ማከናወን እንደተቻለም ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵ ቀይ መስቀል ማኅበር ፋርማሲዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡
ለጤናው ዘርፍ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ከሚያስችሉ የመፍትሄ ርምጃዎች መካከል አንዱ ዲጂታል የጤና ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ለዲጂታል ፈጠራ፣ በተለይ ለዲጂታል ጤና ስርዓት እድገት፣ የፈጠረው እድል የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው፣ የጤና ስርዓቱን በማዘመን ሂደት የግሉ ዘርፍ የመሪነት ሚና ሊኖረው እንደሚገባም አቶ ቢኒያም ገልጸዋል፡፡