በኢትዮጵያ ቻይንኛ ቋንቋን ለሀይስኩል ተማሪዎች መስጠት ሊጀመር ነው

ከቻይና መንግስት ጋር ባለው ግንኙነት መሰረት መስከረም ላይ በሚጀምረው የ2019 ትምህርት ዘመን በፌዴራል ልዩ አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የቻይንኛ ቋንቋ እንዲሰጥ ለማድረግ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ መሆኑን የትምህርት ሚንስቴር ገልጿል።

በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ቻይንኛን የሚያስተምሩ መምህራን ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉም ተብላል።

በትምህርት ሚኒስቴር አጠቃላይ የትምህርት ዘርፍ የትምህርት ፕሮግራሞችና ጥራት ማሻሻል መሪ አስራአስፈፃሚ ዶ/ር ዮሀንስ ወጋሶ የአዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተሻለ ውጤት ያላቸውና በመለያ ፈተና አልፈው የሚገቡ መሆናቸውን አንስተዋል።

እነዚህ ተማሪዎች በአለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማና ስኬታማ እንዲሆኑ ለማድረግም የተለያዩ የውጪ ሀገር ቋንቋዎችን እንዲማሩ እንደሚደረግ ለአሀዱ ሬዲዮ ተናግረዋል።

በተለይም ደግሞ ተማሪዎች የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በውጪ ሀገር የመከታተል እድል ያላቸው በመሆኑ ለዛ እንዲጠቅማቸው የቋንቋ ትምህርቱ እንደሚሰጥ አመላክተዋል።

እንዲማሩ ከሚደረጉት ቋንቋዎች መካከል ደግሞ በቀጣዩ የ2019 የትምህርት ዘመን የቻይንኛ ቋንቋን እንዲማሩ ለማስቻል የዝግጅት ስራዎች እየተጠናቀቁ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከቻይንኛ በተጨማሪም ሌሎች አለምአቀፍ ቋንቋዎችን በማጠናከር የማስተማር ስራው እንደሚቀጥል ዶ/ር ዮሀንስ አስታውቀዋል።
 
 ቻይና አማርኛን ጨምሮ ስዋሂሊ እና ሌሌች የአፍሪካ ቋንቋዎችን በሀገሯ በሚገኙ ዩንቨርሲቲዎች እና ሌሎች ማዕከላት ውስጥ በማስተማር ላይ ትገኛለች።

በኢትዮጵያ ፈረንሳይኛ፣ አረብኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች በዩንቨርስቲዎች ውስጥ በስልጠና መልክ ለተማሪዎች በመሰጠት ላይ ሲገኙ ጀርመንኛ እና ጣልያን ቋንቋዎች ደግሞ በሀገራቱ ኢምባሲዎች አማካኝነት የስልጠና ማዕከላት ውስጥም ይሰጣሉ።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *