የኬንያው አጋካን ዩንቨርስቲ ሆስፒታል ከኢትዮጵያ አቻ ተቋማት ጋር መስራት እንደሚፈልግ ገለጸ

መሰረቱን እስያ ያደረገው እና ኬንያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስክ የተሰማራው አጋካን ዩንቨርስቲ ሆስፒታል በኢትዮጵያ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል።

ሆስፒታሉ በኢትዮጵያ ያሉ የጤና ኢንቨስትመንት አማራጮችን ለመጠቀም ከዩንቨርሲቲዎች እና የጤና ተቋማት ጋር ትብብር በማድረግ ላይ እንደሆነ አስታውቋል።

የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ራሺድ ካላኒ ዛሬ ነሐሴ 14 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በኢትዮጵያ ያለውን የጤና ፍላጎት መጠቀም እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

እንደ ስራ አስኪያጁ ገለጻ ከሆነ አጋካን ዩንቨርስቲ ሆስፒታል በትብብር መስራት ከሚፈልጉ የኢትዮጵያ ጤና እና ኢንቨስትመንት ተቋማት ጋር በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምቶችን በማድረግ ይገኛል።

ለአብነትም በጤና ባለሙያዎች ስልጠና፣ በልምድ ልውውጥ ፣ በጋራ ጥናትና ምርምር ስራዎች ከኢትዮጵያ አቻ ተቋማት ጋር የመስራት ፍላጎት አላቸው።

በየዓመቱ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ለተሻለ ህክምና ወደተለያዩ ሀገራት እንደሚሄዱ እናውቃለን የሚሉት ስራ አስኪያጁ ኢትዮጵያዊያኑ ወደ ናይሮቢ እንዲመጡ የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያዊያን የኬንያ ናይሮቢ ባለው ሆስፒታላችን እንዲመጡ ቀላል ጉዞ እንዲያገኙ ከማድረግ ጀምሮ ተመጣጣኝ የህክምና ፓኬጆችን አዘጋጅተናል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአዲስ አበባ ዋና የበረራ ማዕከል ያለው በመሆኑ ትብብሮችን የማድረግ እቅድ እንዳላቸውም ስራ አስኪያጁራሺድ ተናግረዋል።

አጋካን ዩንቨርስቲ ሆስፒታል በምሥራቅ አፍሪካ ያለውን አገልግሎት ለማጠናከር በኡጋንዳ መንግሥት ግብዣ አማካኝነት አዲስ ዘመናዊ የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል በመገንባት ላይ መሆኑም በስራ አስኪያጁ ተገልጿል።

ኢትዮጵያዊያን ሐኪሞችን መቅጠራቸውን እና ከኢትዮጵያ ለሚመጡ ታካሚዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን እስካሁን ያለው የተገልጋዮች አስተያየት ጥሩ እንደሆነም ተገልጿል።

ዩንቨርሲቲው  በኢትዮጵያም ቅርንጫፍ የመክፈት እቅድ ሊኖረው እንደሚችልም ስራ አስኪያጁ ፍንጭ ሰጥተዋል።

አጋካን ዩንቨርስቲ ሆስፒታል በአፍሪካ እና በእስያ ሀገራት ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት፣ የጤና ምርምርና የሕክምና ትምህርት የሚሰጥ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው።
 
በምሥራቅ አፍሪካ የረጅም ጊዜ ልምድ ያለው ተቃሙ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል የድንገተኛ አደጋ፣ የልብ፣ የካንሰር ሕክምናና ምርመራ እንዲሁም የእናቶችና ሕፃናት ጤና ሕክምና ዋነኞቹ ናቸው።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *