ኢትዮጵያ 12 የጤና ባለሙያዎችን በመንግሥት ለመንግሥት ስምምነት ወደ ባርባዶስ መላኳን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ ተናግረዋል።
ባለሙያዎቹ በባርባዶስ በሕጋዊ መንገድ የሁለት ዓመት ኮንትራት የተፈራረሙ ሲሆን ለዚሁ ተግባር ከሀገሪቱ መንግሥት ጋር የሥራ ሁኔታ እና የክፍያ ስምምነት መደረጉን ሚኒስትር ዴኤታዋ አንስተዋል።
በተጨማሪም “የጤና ባለሙያዎችን በሕጋዊ እና በተደራጀ መንገድ ወደ ውጭ ሀገራት መላክ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፤ የባለሙያ ፍልሰትንም በስርዓት ለመምራት ያግዛል” ማለታቸውን አሀዱ ራዲዮ ዘግቧል።
አጠቃላይ በአፍሪካ የጤና ባለሙያ እጥረት እና የሥራ አጥነት ችግር መኖሩን ያስታውሱት ሚንስትሯ፤ የስልጠና ስርዓትና የሙያ ፈቃድ አሰጣጥን በሀገራት መካከል ማስተሳሰር የሥራ ዕድል ለማስፋት እንደሚረዳ አስረድተዋል።
“የስልጠና እና የሙያ ፈቃድ ስርዓቶች ወጥ እና ተመሳሳይ አለመሆን በባለሙያዎች ላይ እንቅፋት ሲፈጥር ቆይቷል” ያሉ ሲሆን መንግሥት የባለሙያ ፍልሰትን ለመምራትና የሥራ ዕድል ለማስፋት የሁለትዮሽ ትብብሩን እያጠናከረ እንደሆነ ገልጸዋል።
የካሪቢያኗ ባርባዶስ ጠቅላይ ሚንስትር ሚያ አሞር ለሁለት ጊዜ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው ይታወሳል።
በከፊል የሰለጡኑ ዜጎቿን ወደ አረብ ሀገራት ብቻ ስትልክ የቆየችው ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ተለያዩ ሀገራት የሰለጡኑ ዜጎችን በመላክ ላይ ትገኛለች።
ለአብነትም ወደ ጀርመን ፣ ጣልያን፣ ካናዳ እና ሌሎችም ሀገራት የሁለትዮሽ ስምምነት የተፈራረመች ሲሆን ወደተወሰኑት ሀገራት ሰራተኞችን መላክ ተጀምሯል።