ማሰልጠኛ ማዕከሉ የተከፈተው በቻይና እና አፍሪካ የህክምና አጋርነት አማካኝነት ሲሆን ዘመናዊ የሮቦቲክስ ሰርጀሪ ህክምናን በኢትዮጵያ እና ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ለማስፋፋት ያለመእንደሆነ ተገልጿል።በቻይና እና አፍሪካ ትብብር ለአህጉሪቱ የጤና ዘርፍ ማዘመኛ የሚሆን አዲስ የህክምና አጋርነት ፕሮግራም በአዲስ አበባ ሲልከ ሮድ ጄነራል ሆስፒታል ተመርቋል። ሲልክሮድ ሆስፒታል በቻይናዊያን ከአምስት ዓመት በፊት የተቋቋመ ዘመናዊ ሆስፒታል ነው።
በዕለቱ የሮቦቲክስ ሰርጀሪ እና የኢንዶስኮፒክ ቴክኖሎጂ ማሰልጠኛ ማዕከላት የተከፈቱ ሲሆን፣ ኘሮግራሙ አነስተኛ ቀዶ ጥገና ቴክኖሎጂን በስፋት ለማስፋፋት ያለመ ነው።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀስላሴ የዘመናዊ ቴክኖሎጂና የሰለጠነ የሰው ኃይል አስፈላጊነትን ገልጸው፣ የቻይና ባለሙያዎች የሚያደርጉትን የዕውቀትና ክህሎት ሽግግርን አድንቀዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ እና በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይ በበኩላቸው፣ ፕሮግራሙ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን ጠንካራ ወዳጅነት የሚያሳይና ለሌሎች አገልግሎቶች አርአያ የሚሆን መሆኑን ገልጸዋል።
በመጀመሪያው ዙር ስልጠና ከኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ጋና እና ሊቢያ የተጣጣሙ 40 ሰልጣኞች ተሳትፈዋል።
ኢትዮጵያ ኤአይን ለመጠቀም የተለያዩ ስትራቴጂዎችን የቀረጸች ሲሆን የጤና ጉዳዮች ደግሞ ዋነኛው ነው።
ከዚህ በፊት በኤአይ የታገዙ የቲቢ በሽታ ምርመራ እና ህክምና ፣ ድንገተኛ ወረርሽኞችን ለመቆጣጠር እንዲሁም በተመረጡ ሆስፒታሎች በኤአይ የታገዙ የህክምና ማሽኖችን መግጠሟን አስታውቃለች።
ከዚህ በተጨማሪም የኤአይ ዩንቨርስቲ ለማቋቋም የሚንስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን ይህን ተከትሎም ዩንቨርስቲው የሚቋቋምበት ቦታ መረጣ፣ ግንባታ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውም ተገልጿል።