የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢንተርፖልና ከማላዊ ፖሊስ ጋር በመተባበር አደገኛ ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ አድነው ባሻው ውዳሞን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢንተርፖል እና ከማላዊ ፖሊስ ጋር በመተባበር በበርካታ የሀገራችን ወጣቶች ላይ ከባድ ኢሰብአዊ ድርጊት ሲፈጽም የቆየውን አደገኛ ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ አድነው ባሻው ውዳሞን በማላዊ ሀገር በቁጥጥር ሥር እንዲውል በማድረግ ለኢትዮጵያ ተላልፎ መሰጠቱን አስታውቋል።

አድነው ባሻው ውዳሞ በቁጥጥር ሥር ሊውል የቻለው ከግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተለይም ከሀድያ እና ከንባታ ዞኖች በርካታ ወጣቶችን ሕይወት እንደሚያሻሽል በመሐላና በአጉል ተስፋ በማታለል በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲያዘዋውር መቆየቱን ፖሊስ በሰውና በሰነድ ማስረጃ አረጋግጫለሁ ብሏል።
ተጠርጣሪው ከእያንዳንዱ ተጓዥ ከ600 ሺህ እስከ 800 ሺህ ብር ይጠይቃል የተባለ ሲሆን፤ በቅድመ ክፍያ ኢትዮጵያ ውስጥ 100 ሺህ ብር እና ከዚያ በላይ ሲቀበል መቆየቱንም የምርመራ መዝገቡ አመላክቷል።
ተጓዦችን በሞያሌ በኩል ወደ ኬንያ በማሻገርም በጋንቦ ጫካ ውስጥ በድብቅ በማስቀመጥ በየ 24 ሰዓት ትንሽ ሩዝ ከቁራጭ ዳቦ ጋር ብቻ በመስጠት፣ በከፍተኛ ረሃብና የውሃ ጥም እንዲሰቃዩ ከማድረጉም በላይ በሞተርና በእግር ሴሎ በረሃን ጭምር እንዲያቋርጡ አስገድዷቸዋል ሲል ፖሊስ ገልጿል።
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተጎዦችን በሕገ-ወጥ መንገድ ናይሮቢ ከተማ ካደረሳቸውም በኋላ በአንድ ክፍል ውስጥ በማጎር፣ ተጨማሪ ገንዘብ ከቤተሰቦቻቸው እንዲያስልኩ በማስገደድ ከፍተኛ ግፍ መፈጸሙን ፖሊስ በሰውና በሰነድ ማረጃ ደርሼበታለሁ ብሏል።
ከቤተሰብ ገንዘብ ማስላክ ያልቻሉትን ተጓዦችን በመደብደብና “እዚሁ ትሞታላችሁ” እያለ በማስፈራራት እንዲሁም በኤሌክትሪክ ንዝረት በማሰቃየት ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት በመፈጸም ተጨማሪ አንድ መቶ ሺህ ብር እና ከዚያ በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ግብረ አበሮቹ በኩል በባንክ እንዲከፈለው ማድረጉን ፖሊስ ገልጿል።
ከዚህም ባለፈ ተጓዦቹን ከናይሮቢ ወደ ሞምባሳ፣ ከዚያም ወደ ታንዛኒያ በዕቃ መጫኛ ኮንቴነሮች፣ በተሳቢና ከኋላ ክፍት በሆኑና በሸራ በተሸፈኑ መኪኖች ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ተጓዦች በመጫን ታንዛኒያ በሚገኝ ጫካ ውስጥ ጥሎ በመጥፋት ለአሰቃቂ አደጋ ዳርጓቸዋል ሲል ፖሊስ ገልጿል።
አብዛኞቹ ወጣቶች ደቡብ አፍሪካ ሳይደርሱ በተለያዩ ሀገራት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገር በመግባታቸው እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡና እስራቱን ሲጨርሱም እስከ 170 ሺህ ብር ከፍለው ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን የፖሊስ ምርመራ መዝገብ ያመላክታል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢንተርፖል ጋር በመተባበር ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ባደረገው ከፍተኛ ክትትል በበርካታ የሀገራችን ወጣቶች ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊት ሲፈጽምና የኢኮኖሚ ጉዳት ሲያደርስ የቆየውን አድነው ባሻው ውዳሞን የማላዊ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሎ ሐምሌ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ለኢትዮጵያ አሳልፎ መስጠቱን አስታውቋል።