የባህር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ከ157 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ገለጸ

በመካከለኛው ምስራቅ እና በቀይ ባህር ዙሪያ ያለው ጦርነትና ውጥረት ለስራው ፈተና እንደነበር፣ የነዳጅ እጥረትም እንደልብ ለመንቀሳቀስ መቸገርን ጨምሮ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት ፈተና እንደነበሩ አስረድቷል።

የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አብዱልበር ሸምሱ የተቋሙን የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀም እና የ2019 በጀት ዓመት እቅድ በተመለከተ ዛሬ ከሰዓት ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

ዋና ስራ አስፈፃሚው ዓመቱ ለዘርፉ ፈታኝና ከባድ ጊዜ ቢሆንም በብዙ መለኪያዎች ግን የተሻለ ሊባል የሚችል ስራ የተሰራበት እንደነበር ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ ተቋሙ በአጠቃላይ ከ7 ሚሊዮን በላይ ሜትሪክ ቶን ጭነት ማጓጓዝ መቻሉን የተናገሩት ሀላፊው ከዚህ ውስጥ 5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶኑ ከኮንቴይነር ውጪ የሆነ ጭነት፣ 2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶኑ ደግሞ የኮንቴይነር ጭነት እንደሆነ አስረድተዋል።

ከዚህ ጭነት ውስጥ 1.1 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶኑ ጭነት የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ባሉት የራሱ 10 መርከቦች የተጓጓዘ መሆኑን አብራርተዋል።

በየዓመቱ ከውጪ ተገዝቶ የሚገባ የአፈር ማዳበሪያን የማጓጓዝ ሀላፊነት ያለበት ተቋሙ፣ በበጀት ዓመቱ 2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ አጓጉዞ ማስገባቱን ጠቅሷል።

ጅቡቲ ወደብ የደረሰውን ማዳበሪያ 26 በመቶውን በባቡር፣ ቀሪውን 74 በመቶ በጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ መጨረሻ መዳረሻቸው ማድረሱን አስታውሷል።

የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ በበጀት ዓመቱ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ካሉት 10 መርከቦች በተጨማሪ 47 መርከቦችን በመከራየት እንዲሁም ከ7 መሰል የመርከብ ድርጅቶች (ላይነርስ) ጋር በመተባበር ስራውን መስራቱን ተናግረዋል።

ጭነትን ከወደብ ወደ ደረቅ ወደቦችና ወደ መጨረሻ መዳረሻቸው ለማጓጓዝም 665 የራሱን ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች እንዲሁም 3,643 ከተቋሙ ውጪ ያሉ የጭነት ተሽከርካሪዎችን በማሰማራት ስራውን መከወን ተችሏል ተብሏል።

በበጀት ዓመቱ ተቋሙ ከሰራው ስራ 157.2 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ማስገባት የቻለ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከታክስ በፊት የተገኘው ትርፍ 28.2 ቢሊዮን ብር መሆኑ ተነግሯል።

በበጀት ዓመቱ የተገኘው ገቢም ከእቅዱ በላይ 108.5 በመቶ አፈፃፀም ያሳየ መሆኑን ያብራሩት ስራ አስፈፃሚው፣ ቀድሞ ታቅዶ የነበረው 144.9 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ማስገባት እንደነበር ተናግረዋል።

ዓመቱ በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት እና በቀይ ባህር ዙሪያ ባለ ውጥረት ፈታኝ እንደነበር ያስረዱት ሀላፊው፣ ተቋሙ ካሉት አስር መርከቦች “ጊቤ” የምትሰኘው በሆርሙዝ ሰርጥ ተዘግቶባት ለአራት ወራት በመቆየቷ ከፍተኛ ገቢ እንዲያጡ ማድረጉን ጠቁሟል።

መርከቧ ለአራት ወራት በመቆየቷ ከደረሰው የገቢ ማጣት ውጪ በመርከበኞች፣ በመርከቧ እና በጭነቱ ላይ ግን የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ተናግረዋል።

ጦርነቱ በፈጠረው የነዳጅ እጥረት ለጭነት ተሽከርካሪዎች ብቻ ሳይሆን መርከቦችን ለማንቀሳቀስም የነዳጅ እጥረት አጋጥሞ እንደነበር ተናግረዋል።

ተቋሙ በመጪው አምስት ዓመት እሰራዋለሁ ብሎ በቀረፀው ስትራቴጂ ተጨማሪ 16 መርከቦችን ለመግዛት ማቀዱንም አስረድቷል።

በእቅዱ መሰረት የመጀመሪያዎቹን ስድስት መርከቦች ግዢ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለመፈፀም አስቀድሞ ታቅዶ የነበረ ሲሆን፣ “የግዢው ሂደት ከምን ደረሰ?” ስንል ዋና ስራ አስፈፃሚውን ኢንጂነር አብዱልበርን ጠይቀናል።

እሳቸውም በተለያዩ ምክንያቶች የግዢ ሂደቱ ባይጠናቀቅም ግዢውን የተመለከተው ዝርዝር ስራ ግን መጀመሩን ነግራናል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ግዢውን ማሳካት ባይቻልም በ5 ዓመት ጊዜ ውስጥ ግን የ16ቱ መርከቦች ግዢ ይሳካል ብለው እንደሚያስቡ መልሰዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *