ትምህርት ሚንስቴር በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን እንደማይመድብ ገለጸ

በትግራይ ክልል ባለው ነባራዊ ሁኔታ በክልሉ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች በክልሉ አስቻይ ሁኔታ እስኪፈጠር በሌሎች የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች በጊዚያዊነት እንዲመደቡ መወሰኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አስታውቀዋል።

ሚኒስትሩ በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ይማሩ የነበሩና በአሁኑ ወቅት በክልሉ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ትምህርታቸውን መቀጠል ባለመቻላቸው ለቅሬታቸው መፍትሔ ለመጠየቅ በትምህርት ሚኒስቴር ግቢ ከተገኙ ተማሪዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ወቅት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንደገለጹት፣ በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች ደህንነታቸው ወደሚጠበቅባቸው ሌሎች የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች በጊዚያዊነት ተመድበው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ትምህርት ሚኒስቴር መወሰኑን ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም፣ ወጣቶች በአሁኑ ወቅት ማተኮር ያለባቸው በትምህርታቸው ላይ በመሆኑና ወደፊት ሀገራቸውን የሚረከቡ ዜጎች እንዲሆኑ ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን ጠቁመዋል።

ሀገር ማጽናት የሚቻለው የዛሬው ትውልድ ለነገው ትውልድ ማሰብ ሲጀምር ነው ያሉት ሚኒስትሩ ጦርነትና ግጭትን በመሸሽ ከትግራይ ክልል የወጡ ተማሪዎች በሰላም የመኖርና የመማር መብት ያላቸው መሆኑን አስገንዝበዋል።

በመሆኑም እነዚህን የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች በተለያየ መንገድ ማስተናገድና ትምህርታቸውን ያለመስተጓጎል እንዲቀጥሉ ማድረግ ተገቢ መሆኑን
ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

በዚህም ተማሪዎች ለምዝገባ በአካል ወደ ትምህርት ሚኒስቴር መምጣት ሳይጠበቅባቸው ከዛሬ ማታ ጀምሮ ይፋ በሚደረገው የበየነ መረብ (Online) መተግበሪያ በመጠቀም መመዝገብ እንደሚችሉ አስታውቀዋል።

በምዝገባው ወቅትም ተማሪዎች ከዚህ በፊት ይማሩበት የነበረውን ዩኒቨርስቲ፣ የትምህርት ዘመናቸውን እና የሚማሩበትን የትምህርት መርሐ ግብር (field of study) በመግለጽ ባሉበት ቦታ ሆነው የዝውውር ፎርሙን በአጭር ግዜ እንዲሞሉ አሳስበዋል።

ዛሬ በአካል በትምህርት ሚኒስቴር ግቢ የተገኙት በርካታ ተማሪዎች የተለያዩ ጥያቄዎች ያቀረቡ ሲሆን ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወትን ጨምሮ ሌሎች የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሚንስቴሩ ከዚህ በፊት የክልሉ መንግሥት ዩንቨርሲቲዎችን ከጦር መሳሪያ ማከማቻ እና ግጭት ቀጠና ነጻ እንዲያደርግ ማሳሰቡ ይታወሳል።

በትግራይ ክልል በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አማካኝነት የተመሰረተው ጊዜያዊ አስተዳድር በሀይል ከፈረሰበት ጊዜ ጀምሮ በአካባቢው አዲስ የጦርነት ስጋት እየጨመረ ይገኛል።

የህወሀት ታጣቂዎች ወደ አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ተዋጊዎችን እና የወታደሮችን እንቅስቃሴ መጨመሩን ተከትሎ የፌደራል መንግሥት የድሮን ጥቃት በተደጋጋሚ በመፈጸም ላይ ይገኛል።

የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሰብዓዊ መብት ጥበቃ ተቋማት የፌደራል መንግሥት እና ህወሀት ወደ ግጭት እንዳይገቡ በማሳሰብ ላይ ናቸው።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *