የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በተለያዩ በዲጂታል የንግድ መንገዶች አማካኝነት በብር የሚከናወኑ የሰው-ለሰው (P2P) የገንዘብ ዝውውሮች እና የክሪፕቶ ከረንሲ ግብይቶች ሕገ-ወጥ መሆናቸውን አስታውቋል።
ባንኩ ዛሬ የካቲት 20 ቀን 2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፣ በማንኛውም መድረክም ሆነ የልውውጥ ማዕከል በብር የሚደረጉ የዲጂታል ሀብት ግብይቶች ያለ ባንኩ ፈቃድ በፍጹም የተከለከሉ መሆናቸውን አስታውቋል።
ይህ እገዳ ማንኛውንም በብር የሚሰላ የክሪፕቶ ከረንሲ ልውውጥን የሚያካትት መሆኑም ተገልጿል።
እንደ ብሔራዊ ባንክ ማብራሪያ፣ እነዚህ መድረኮች ለከፍተኛ የዋጋ መዋዠቅ፣ ለገንዘብ ማጭበርበር እና ለውጭ ምንዛሪ ዋጋ መዛባት እጅግ ተጋላጭ ናቸው።
በተጨማሪም እንደ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን የመሳሰሉ የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ ሥርዓቶች በእነዚህ መድረኮች ላይ ባለመኖራቸው ኅብረተሰቡ ለከፍተኛ አደጋ ሊጋለጥ እንደሚችል ተጠቁሟል።
በቅርቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንዳንድ የፒር-ቱ-ፒር መድረኮች በገጠማቸው የቴክኒክ እና የፋይናንስ ችግር ምክንያት ተጠቃሚዎች ገንዘባቸውን እንዳያገኙ መከልከላቸው ለዜጎች እንደ ትልቅ ማስጠንቀቂያ ተጠቅሷል።
ባንኩ በአሁኑ ወቅት ደህንነቱ የተጠበቀ እና ሥርዓት ያለው የዲጂታል ፋይናንስ ተሳትፎ እንዲኖር የሚያስችል አጠቃላይ የቁጥጥር ማዕቀፍ ለማዘጋጀት ከዓለም አቀፍ አቻ ተቋማት ጋር እየመከረ መሆኑን ገልጿል።
ይሁን እንጂ ይህ ሕጋዊ ማዕቀፍ በይፋ ሥራ ላይ እስኪውል ድረስ ማንኛውም በብር የሚደረግ የክሪፕቶፕ ዝውውር በሕግ እንደሚያስጠይቅ ባንኩ በድጋሚ አረጋግጧል።
ብሔራዊ ባንክ ከዚህ በፊት የምናባዊ ግብይቶችን በይፋ የከለከለ ሲሆን በቀጣይ ግብይቱ የሚመራበትን መመሪያ ይፋ እንደሚያደርግ መግከጹ ይታወሳል።
በኢትዮጵያ የክሪፕቶ ግብይቶችን ለማድረግ የተቋቋሙ ከ10 በላይ ዓለም አቀፍ የመረጃ ማዕከላት (ዳታ ማይኒንግ) ያሉ ሲሆን የሀገሪቱን ኤሌክትሪክ በባበጠቀም ከ30 በመቶ በላይ ድርሻ ይዘዋል።
ርካሽ የኤሌክትሪክ ሀይል ፍለጋ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት እነዚህ የመረጃ ማዕከላት ፍጆታቸው መጨመሩን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት የታሪፍ ጭማሪ ማድረጉን ከሁለት ወር በፊት አስታውቋል።