የብልጽግና ፓርቲ ከነጋዴው ማህበረሰብ በአስገዳጅነት ገንዘብ መሰብሰቡን እንዲያቆም ተጠየቀ

ለሰባተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በምርጫው የሚሳተፍ ሀገር አቀፍ እና ክልላዊ ፓርቲዎች በምርጫው ላይ ጉልህ ተሳትፎ ለማድረግ የድርሻቸውን ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ።

ከዝግጅቶቻቸው መካከልም ዋነኛው ለምርጫው የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ እና ሀብት ከአባላቶቻቸው እና ከደጋፊዎቻቸው በተቀመጠው የህግ አግባብ መሰረት ማሰባሰብ አንዱ መሆኑን ኢዜማ ገልጿል።

ይህ የገንዘብ እና ቁሳቁስ ማሰባሰብ ሂደት የአገሪቱን የፋይናንስ አሰራር ስረዓት እንዲሁም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፓለቲካ ፓርቲዎች የሀብት አሰባሰብን በተመለከተ ያስቀመጣቸውን ጥብቅ የህግ ድንጋጌዎች ባከበረ መልኩ መሆን እንዳለበትም ፓርቲው አስታውቋል።

ኢዜማ በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ ብልፅግና ፓርቲ የህግ ድንጋጌዎች በጣሰ መልኩ በማንአለብኝነት መንፈስ ከፍተኛ ገንዘብ አባል ካልሆኑ ነጋዴዎች እና ባለሀብቶች በግዳጅ እያሰባሰበ እንደሆነ ደርሼበታለሁ ብሏል።

“16 ሚሊዮን አባል አለኝ የሚለው ብልፅግና ፓርቲ የመንግሥትን መዋቅር ተቆጣጥሮ የመንግሥትን ሀብት በግልጽና በሥውር መጠቀሙ ሳያንስ የኑሮ ጫና ያጎበጣቸውን የመንግሥት ሠራተኞችን ለድርጅት በሚል ሰበብ ለፓርቲው በላባቸው ለፍተው ሊያገኙ የሚገባውን ከደመወዛቸው እየቆረጠ ሲያስቀር ሰንብቷል” ሲልም ኢዜማ ስሞታ አሰምቷል።

ከሰሞኑን ደግሞ በተለየ ሁኔታ በፍቃደኝነት ከሚለግሱት ባለሀብቶች አልፎ በየክፍለ ከተማው እና በወረዳዎች በአካል በመሔድ እና በስልክ በማስፈራራት ጭምር ለምርጫው የገንዘብ ድጋፍ ማሰባስብ ሂደት ውስጥ መግባቱ ከህግም ሆነ ከሞራል ያፈነገጠ እና ሕገወጥ ተግባር መሆኑንም አስታውቋል።

የንግዱ ማህበረሰብ በብልፅግና የተሳሳተ የግብር ፖሊሲ ምክንያት ከሰራው እና ካተረፈው በላይ ግብር እንዲከፍል እየተጠየቀ ጀርባው መጉበጡ ሳያንስ በማስፈራራት አባል ያልሆኑበት ድርጅትን በገንዘብ ደግፍ መባሉ እጥፍ ድርብ በደል ነው በመሆኑ እንዲቆም ጠይቋል ።

ብልጽግና ገዢ ፓርቲ በመሆኑ ብቻ ድጋፍ ለማድረግ ፍፁም ፈቃደኛ የሆኑ ባለሀብቶችና ግለስቦች እንዳሉ እናምናለን ያለው ኢዜማ ይህን በአግባቡ ከመጠቀም አልፎ የመንግሥት መዋቅር በእጄ ነው በሚል ተገቢ ያልሆነ ማን አለብኝነት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ዛሬን ሳይሆን ነጋችንን ከመጉዳት ባለፈ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ተስፋን እንደሚያጨልም አስታውቋል።

ኢዜማ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የድርሻቸውን እንዲያወጡ ፍላጎት አለው፣ ሁሉ በእጁ የሆነ ገዢ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ሊጠቀሙበት የሚችል የምርጫ ፈንድ ቢቃቋም ተገቢ ነው ብሎ ያምናል።

ገዢው ፓርቲ ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት ያለኝ ይበቃኛል በማለት ሌሎች ፓርቲዎችን ዜጎች እንዲያግዙ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱን ደግፉ ብሎ በይፋ መግለጫ እንዲሰጥና እንዲያበረታታ ሲጠበቅበት በእዚህ አይነቱ ህገወጥ ተግባር መሰማራቱ እጅግ አስነዋሪ መሆኑን በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

ብልጽግና ለዴሞክራሲ ሥረዓት ግንባታ ያለው የተንሸዋረረ ግንዛቤ እንዲሻሻል እና ከኢ-ዴሞክራሲያዊ አካሂዶች እንዲቆጠቡ ሲልም ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል።

ህግን እንዲያስከብር እና እንዲያከብር ስልጣን የተሰጠው የመንግስት አካል የተሰጠውን ስልጣን ተገን በማድረግ የዴሞክራሲ ስረዓትን በሚያቀጭጭ መንገድ የሀገርን እና የህዝብን ሀብት ለፓርቲ ዓላማ የማዋል ተግባሩን በፅኑ እንደሚያወግዝ አስታውቋል።

ይሁንና በኢዜማ ክስ የቀረበበት ብልጽግና ፓርቲ እስካሁን ስልጣንን በመጠቀም ከነጋዴዎች እና የመንግስት ሰራተኞች ሀብት አሰባስቧል ተብሎ ለተነሳበት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።

ሰባተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የመራጮች ድምጽ መስጫ ቀን የፊታችን ግንቦት 24፣ 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተገልጿል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *