ሳውዲ አረቢያ በኢትዮጵያዊያን ላይ የሞት ፍርደኞችን በስቅላት እንዳትቀጣ ተጠየቀ

የአፍሪካ የሰዎችና ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ በኢትዮጵያዊያን ላይ የተላለፉ ፍርዶችና የሞት ቅጣቶች እንደገና እንዲታዩ “ሁሉንም መንገዶች” እንዲጠቀምና የሞት ፍርድ የተፈረደባቸውን ኢትዮጵያዊያን ደኅንነት ለማስከበር አስፈላጊ “የዲፕሎማቲክ” እና “የቆንስላ” ርምጃዎችን እንዲወስድ ጠይቋል።

ተቋሙ ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ በበርካታ ኢትዮጵያዊያን ላይ የተጣለው የሞት ቅጣት በእጅጉ እንዳሳሰበው አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ኢትዮጵያዊያኑ “የሕግ ውክልና” እና የፍርድ ቤት “የትርጉም አገልግሎት” እንዲያገኙና ከቤተሰባቸው ጋር እንዲገናኙ ጥረት እንዲያደርግ፤ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ፍልሠተኞችን መብት “በሁለትዮሽ ግንኙነቶች” እና በጠንካራ “የቆንስላ ድጋፎች” እንዲያስከብርም ኮሚሽኑ ጠይቋል።

ሳውዲ አረቢያ የሞት ፍርድ በስፋት ከሚፈጸምባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን በያዝነው ዓመት ብቻ ቢያንስ 12 ኢትዮጵያዊያን የሞት ፍርድ ተፈጽሞባቸዋል።

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዎች፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና ሌሎችም የሀገር ውስጥ እና ሌሎች ድርጅቶች ሳውዲ አረቢያ ለኢትዮጵያዊያን ምህረት እንድታደርግ እየጠየቁ ይገኛሉ።

እንደ ሂውማን ራይትስ ዎች ሪፖርት ከሆነ ቢያንስ 52 ኢትዮጵያዊያን የሞት ፍርድ ተላልፎባቸው በሳውዲ አረቢያ እስር ቤቶች ውስጥ ያሉ ሲሆን ሪያድ ፍርዱን ከመፈጸም እንድትቆጠብ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚንስቴር በበኩሉ በሳውዲ አረቢያ እስር ቤት ያሉ ዜጎችን ደህንነት በመከታተል ላይ መሆኑን ገልጾ ከሀገሪቱ መንግሥት ጋርም በጋራ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ከ1 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በሳውዲ አረቢያ ምህረት አማካኝነት ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ይታወሳል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *