የደቡብ ኮሪያው የኤሌክትሮኒክስ ግዙፍ ኩባንያ ኤልጂ (LG)፣ በኮሪያ ጦርነት ወቅት ለተሳተፉት የኢትዮጵያ ቃኝው ሻለቃ ዘማቾች የልጅ ልጆች ለተዋቀረው “ቃኝው ክዋየር” ዘመናዊ የልምምድ ስቱዲዮ ሊገነባ መሆኑን አስታውቋል።
ስቱዲዮው በአዲስ አበባ በሚገኘው የኮሪያ አርበኞች መታሰቢያ ህንፃ ውስጥ የሚገነባ ሲሆን፣ የድምፅ መከላከያ ፣ ዘመናዊ የድምፅ ሲስተም እና ዲጂታል የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች እንደሚሟሉለት ተገልጿል።
ኤልጂ ይህንን የበጎ አድራጎት ፕሮጀክት የሚያከናውነው ከኮሪያ የሀገር ፍቅርና የአርበኞች ጉዳይ ሚኒስቴር እና “Warm Mind” ከተባለው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር ነው።
በ2018 የተቋቋመው ይህ የሙዚቃ ቡድን፣ እስካሁን ድረስ ቋሚ የልምምድ ቦታ ባለመኖሩ እና የቴክኖሎጂ ቁሳቁስ እጥረት በነበረበት ሁኔታ የባህል አምባሳደር በመሆን የኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃዎችን እና እንደ “አሪራንግ” ያሉ የኮሪያ ታዋቂ ዜማዎችን በኦፊሴላዊ መድረኮች ሲያቀርብ ቆይቷል።
በተጨማሪም ኤልጂ ለቡድኑ አባላት ሙሉ የጉዞ እና የወጪ ስፖንሰርሺፕ በማዘጋጀት በሴኡል የኮሪያ ጦርነት ስምምነት መታሰቢያ በዓል ላይ እንዲዘፍኑና የኤልጂ ሳይንስ ፓርክን እንዲጎበኙ አድርጓል።
የኮሪያ መንግስት ኤልጂ ለኢትዮጵያውያን አርበኞች ዘሮች እና የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲ እያደረገ ላለው ድጋፍ ይፋዊ የክብር ምስክር ወረቀት አበርክቶለታል።
ኤልጂ ከ2014 ጀምሮ በኢትዮጵያ ነፃ የሙያና ቴክኒክ ስልጠና የሚሰጠውን “LG-KOICA Hope TVET College” በማቋቋም ሲደግፍ መቆየቱ ይታወሳል።