የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን እንዳስታወቀው የአዲስ ስታንዳርድ የበየነ-መረብ መገናኛ ብዙኃን ምዝገባ ምስክር ወረቀት ከየካቲት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ተሰርዟል ብሏል፡፡
እንደ ባለስልጣኑ መግለጫ ከሆነ አዲስ ስታንዳርድ የበየነ-መረብ መገናኛ ብዙኃን የሚዲያ ስነ ምግባርን፣ የኢትዮጵያ ሕጎች እና የሀገርንና የሕዝብን ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ ዘገባዎችን በተደጋጋሚ በማሰራጨት ላይ ይገኛል ሲል አስታውቋል፡፡
በመሆኑም ባለሥልጣኑ ይህንኑ ድርጊት በመመርመር አዲስ ስታንዳርድ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን እንዲታረም እና ከአጥፊ አካሄዱ እንዲቆጠብ በተደጋጋሚ ምክር ሲሰጥ ቢቆይም ለመታረም ፈቃደኛ ሳይሆን በመቅረቱ ፈቃዲ እንደተሰረዘ ባለስልጣኑ ገልጿል።
በተጨማሪም በሚዲያ ዘርፉ ላይ የሙያ ስነምግባር እና የሀገርና የህዝብ ብሔራዊ ጥቅም አክብሮ እንዲሰራ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ እና ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም ለመታረም ፈቃደኛ አልሆነም ያለው ባለስልጣኑ የአዲስ ስታንዳርድ የበየነ-መረብ መገናኛ ብዙኃን የምዝገባ ምስክር ወረቀት በመገናኛ ብዙኃን አዋጁ መሰረት ከዛሬ የካቲት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ተሰርዟል፡፡
ከዚህ እለት አንስቶም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የአዲስ ስታንዳርድ የበየነ-መረብ መገናኛ ብዙኃን የምዝገባ ምስክር ወረቀት እንደተሰረዘ እና ምንም አይነት የሚዲያ ፈቃድ እና እውቅና እንደሌለው አስታውቋል፡፡
ፈቃዱ እንደተሰረዘበት የተገለጸው አዲስ ስታንዳርድ በበኩሉ በኢትዮጵያ ብዙኃን መገናኛ ባለስልጣን የቀረበበትን ክስ ውድቅ አድርጓል።
ሚዲያው እንዳስታወቀው በሚያስተላልፋቸው ይዘቶች ዙሪያ እስካሁን ከባለስልጣኑ የደረሰው ማስጠንቀቂያ አለመኖሩን እና ሚዛናዊ ያልሆኑ ዘገባዎችብ አስተላልፏል በሚል የተጠሰው ክስም ሐሰተኛ ነው ሲል አስታውቋል።