የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ዱባይ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት በኢትዮጵያውያን ላይ ኢሰብአዊ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ የነበሩ ዳውድ ተፈሪ እና ደስታ ተገኝ የተባሉ አደገኛ ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።
ተጠርጣሪዎቹ የማታለያ ዘዴዎችን በመጠቀም 105 ዜጎችን በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ዱባይ በመውሰድና ከ188 ሚሊየን ብር በላይ ከተጎጂዎች በመሰብሰብ፣ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲፈጽሙ የቆዩ በመሆናቸው ከዱባይ ፖሊስ ጋር በመተባበር በቁጥጥር ሥር ውለው ለኢትዮጵያ ተላልፈው እንዲሰጡ ተደርጓል ብሏል።
ተጠርጣሪዎቹ ዱባይ ተቀምጠው ሀገር ውስጥ ባሉ ተባባሪዎቻቸው አማካኝነት ወጣቶችን በመመልመል ወደ ዱባይ በመላክ፣ በተዘጋጀ የማገቻ ቦታ በማቆየት፣ በተለይ በሴቶች ላይ ጥቃት በማድረስና በማሰቃየት ከፍተኛ ወንጀል ሲፈጽሙ የቆዩ መሆናቸው ተረጋግጧል።
ፌደራል ፖሊስም ጉዳዩን ሲያጣራ ቆይቶ በሀገር ውስጥና በውጭ ሆነው በተቀናጀ መንገድ ወንጀሉን ሲፈፅሙ በቆዩት ተጠርጣሪዎችና በግብረ አበሮቻቸው ላይ የፍርድ ቤት መያዣ ትዕዛዝ በማውጣት ከዱባይ ፖሊስ ጋር በትብብር በመስራት በቁጥጥር ሥር ውለው ለሀገራችን ተላልፈው እንዲሰጡ ማድረጉንም ገልጿል።
ተጠርጣሪዎቹ ሰውን ወደ ውጭ መላክ የሚያስችል ሕጋዊ ፍቃድ ሳይኖራቸው፣ በሀገር ውስጥ ያለው ቡድን ከውጪ ካለው ቡድን ጋር ትስስር በመፍጠር “በተለያዩ ኩባንያዎች እናስቀጥራችኋለን’’ በማለት ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ዜጎችን በመመልመል፣ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨትና ያልተገባ ተስፋ በመስጠት ለኪሳራና ጉዳት ዳርገዋል ተብሏል።
በዚህም ከአንድ ሰው ከ320 ሺህ እስከ 600 ሺህ ብር በመቀበል ማታለያ የቱሪስት ቪዛ አዘጋጅተው በመላክ፣ በሀገር ውስጥ ባሉ ተባባሪዎቻቸው በተከፈተ የባንክ አካውንት ገንዘቡን በኢትዮጵያ ብር፣ በድርሃም እና በሳውዲ ሪያል ገቢ የሚያስደርጉ መሆናቸውን ፖሊስ ደርሶበታል።
ገንዘቡን የከፈሉ ተጎጂዎች ዱባይ እንደገቡ በጉልበት ሥራ ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ፣ ከተጎጂዎች “ኮሚሽን” በሚል ተጨማሪ ገንዘብ በማስከፈል እንዲሁም የሁለት ወር የቱሪስት ቪዛ ሲያልቅ “የሁለት ዓመት የመኖሪያ ፍቃድ እናሰጣችኋለን፤ ካልከፈላችሁ ግን ወደ ኢትዮጵያ ትመለሳላችሁ” በማለት በአንድ ሰው 1 ሺህ 200 ድርሃም እንዲከፍሉ በማድረግ ግፍና ስቃይ ሲያደርሱ ቆይተዋል ብሏል ፖሊስ።
ተጠርጣሪዎቹ ተጎጂዎችን ከዱባይ ኤርፖርት ከተቀበሉ በኋላ ሰዎችን የሚያከማቹበት ቦታ በመውሰድ፣ በአንድ ክፍል ውስጥ በርካታ ወንዶችንና ሴቶችን በማገት ለከፍተኛ ርሃብ እና እንግልት እንዲሁም ሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃት ሲያደርሱባቸው መቆየታቸውን ፖሊስ ገልጿል።
በተጨማሪም በሀገር ውስጥ ሆነው ዱባይ ካሉት ግብረ-አበሮቻቸው በሚሰጣቸው ትዕዛዝ ሰዎችን መልምሎ በመላክና የባንክ አካውንት ከፍተው ገንዘብ እያሰባሰቡ የነበሩ 1ኛ ብዙአየሁ አውግቸው እና 2ኛ ራህመት አበበ የተባሉ ተጠርጣሪዎችን ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራውን በማከናወን ላይ መሆኑን ገልጿል።
ፖሊስ ምርመራውን ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂዎች ተጠቅሞ ይህንን ውስብስብና ድንበር ተሸጋሪ ወንጀል ለማጣራት እንዲሁም በእነዚህ ተጠርጣሪዎች አማካኝነት ከሀገር ወጥተው ከፍተኛ ስቃይ ደርሶባቸው ከነበሩ ግለሰቦችና ተጎጂዎች ካሉበት ዱባይ የቀጥታ ቨርቹዋል የምስክርነት ቃላቸውን በመቀበል ላይ ይገኛል።
ፖሊስ ሕጋዊ ፍቃድን ሽፋን በማድረግ ከሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ጋር በመመሳጠር ሕገ-ወጥ ተግባር የሚፈጽሙና በዜጎች ከፍተኛ ኢሰብዓዊ ድርጊት የሚፈጽሙ ኤጀንሲዎችም መኖራቸውን ማረጋገጡን ጠቅሶ በቀጣይ ምርመራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በዚህ ውስብስብ ወንጀል ውስጥ በህጋዊ ሽፋን ህገ-ወጥ ተግባር የሚፈጽሙ አካላትን ለመያዝ ከዱባይ ፖሊስና በዱባይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በቅንጅት በመስራት ህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ላይ ጠንካራ ክትትል እያደረገ መሆኑን ገልጿል።