ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እሁድ ዕለት ኢራን በኩዌት ላይ የፈጸመችውን ጥቃት ተከትሎ ከኩዌት ልዑል አልጋ ወራሽ ሼክ ሳባህ ኻሊድ አል ሀማድ አል ሳባህ ጋር በስልክ መወያየታቸው ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከኩዌቱ ልዑል አልጋ ወራሽ ጋር ባደረጉት ውይይት በአገሪቱ ሉዓላዊ ግዛት እና የአየር ክልል ላይ የሚፈጸም ጥቃትን በጽኑ ማውገዛቸውን የኩዌት የዜና ወኪል ዘግቧል።
ይህ በዚህ እንዳለም ኢራን በእስራኤል እና አሜሪካ በደረሰባት የአየር ላይ ጥቃት የአጸፋ እርምጃ በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ላይ በምትወስዳቸው እርምጃዎች ኢትዮጵያዊን መጎዳታቸው እየተገለጸ ይገኛል፡፡
በመቶ ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊን እስራኤልን ጨምሮ በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ተቀጥረው በመስራት ላይ ሲሆኑ ሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬት፣ ኳታር፣ ኩዌት እና ባህሬን ብዙ ኢትዮጵያዊያን ይኖራሉ፡፡
ኢራን የአሜሪካ ጦር መገኛ ናቸው ባለቻቸው የአካባቢው ሀገራት ላይ የሚሳኤል እና ድሮን የታገዙ እርምጃ በመውሰድ ላይ ስትሆን በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ላይ በፈፀመችው ጥቃት የኢትዮጵያዊ ዜጋ ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል፡፡
የካቲት 21 ቀን 2018 ዓ.ም የተጀመረውን ተከታታይ የኢራን የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃት ተከትሎ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጉዳት ከደረሰባቸው 58 ሰዎች መካከል ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙበት የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አረጋግጧል። ይሁን እንጂ ጥቃቱ በደረሰባቸው የኢትዮጵያ ዜጎች ቁጥር ላይ ሚኒስቴሩ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።
እንደ ሚኒስቴሩ መግለጫ ከሆነ፣ ጥቃቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የኤምሬትስ የአየር መከላከያ ሥርዓት ከኢራን የተተኮሱ 165 ባሊስቲክ ሚሳኤሎችን፣ ሁለት የክሩዝ ሚሳኤሎችን እና 541 ድሮኖችን ማክሸፍ ችሏል።
ከጥቃቱ በኋላ በሁለተኛው ቀን ብቻ የኤምሬትስ አየር ኃይል እና የአየር መከላከያ ክፍሎች 20 ባሊስቲክ ሚሳኤሎችን ያወደሙ ሲሆን፣ ስምንቱ ባሕር ውስጥ መውደቃቸው ተገልጿል። በተጨማሪም ሁለት የክሩዝ ሚሳኤሎች እና 311 ድሮኖች በአየር ላይ የተመቱ ቢሆንም፣ 21 ድሮኖች ግን በሲቪል ተቋማት ላይ ማረፋቸውን ሚኒስቴሩ ይፋ አድርጓል።
ከየካቲት 21 ጀምሮ ወደ ኤምሬትስ አቅጣጫ ከተወነጨፉ 165 ባሊስቲክ ሚሳኤሎች መካከል 152ቱ ሲወድሙ፣ 13ቱ ደግሞ ባሕር ውስጥ መውደቃቸው ተመልክቷል።
ከተለዩት 541 ድሮኖች መካከልም 506ቱ በአየር ላይ የተመቱ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 35 ድሮኖች በኤምሬትስ ግዛት ውስጥ በመውደቅ በንብረት ላይ ጉዳት አድርሰዋል።
ይህ መጠነ ሰፊ ጥቃት የፓኪስታን፣ የኔፓል እና የባንግላዴሽ ዜግነት ያላቸውን ሦስት ግለሰቦች ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን፣ በሌሎች 58 ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት አድርሷል ተብሏል።
የመካለኛው ምስራቅ ጦርነት በኢትዮጵያ ላይ ቀጥተኛ የተባለ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን በተለይም በበርካታ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በቀን ተደጋጋሚ የመንገደኞች እና የጭነት በረራ ያለው ሲሆን በጦርነቱ ምክንያት በረራዎቹ ላልተወሰነ ጊዜ በመራዘማቸው ህም በሀገሪቱ ገቢ ላይ ጉዳት በማድረስ ላይ ነው ተብሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በጦርነቱ ምክንያት የዓለም ነዳጅ እና ምግብ ዋጋ እንዲያሻቅብ በማድረጉ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ቀጥተኛ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል፡፡