ባንኮች የከፈቷቸውን አካውንቶች በሁለት ሳምንት ውስጥ ከብሔራዊ መታወቂያ (ፋይዳ) ጋር የማስተሳሰር ሥራ እንዲያጠናቅቁ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል።
ብሔራዊ ባንክ እና የብሔራዊ መታወቂያ በጋራ ባወጡት አዲስ የአተገባበር ሥርዓት መሰረት የፋይናንስ ተቋማት ብሄራዊ ኦፕሬተር በሆነው ኢት-ስዊች በኩል ከብሔራዊ መታወቂያ (ፋይዳ) ጋር የማስተሳሰር ሥራ መስራት መጀመራቸው ተገልጿል።
እስካሁን 10 የሚሆኑ የፋይናንስ ተቋማት ከብሔራዊ መታወቂያ (ፋይዳ) ጋር የማስተሳሰሩን ሥራ ጨርሰዋል ሲባል ሌሎች ባንኮች በሙከራ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ይለበስ አዲስ ለኢትዮ ነጋሪ እንደገለጹት ይህ አሰራር ባንኮች አገልግሎታቸው ቀልጣፋ እንዲሆንና ማዕከላዊ የመረጃ አያያዝ እንዲኖር ያስችላል ሲሉ ገልጸዋል።
አክለውም ትስስሩ ባንኮች ከደንበኞቻቸው ጋር ያላቸውን አገልግሎት ያሳልጥላቸዋል፤ ወጪንም ይቆጥብላቸዋል ብለዋል፡፡
የኢት-ስዊች ቺፍ ፖርት ፎልዮ ኦፊሰር (CPO) አቤኔዘር ወንደሰን በበኩላቸው ከዚህ በፊት ደንበኞች አካውንት ሲያወጡ ባንኮች የደንበኛውን መታወቂያ ለማረጋገጥ ሁለት መቶ ብር በአንድ ሰው ክፍያ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
በአዲሱ አሰራር ባንኮች ስንት እንደሚከፍሉ ተመን ባይወጣላቸውም ክፍያው ሲወሰን ከሀምሳ ብር እንደማይበልጥና ይህም ባንኮችን ከብዙ ወጪ እንደሚያድናቸው ተናግረዋል።
ባንኮች እስከ ህዳር አጋማሽ ድረስ አስተሳስረው መጨረስ እንዳለባቸውም ነው አቤኔዘር ገልጸዋል።
ባንኮቹ ከብሔራዊ መታወቂያ ጋር በቀጥታ ትስስር አይኖራቸውም ሲባል ትስስር የሚኖራቸው በኢት-ስዊች በኩል እንደሆነም ተገልጿል።
ኢት-ስዊች ሁሉንም ባንኮች ያስተሳሰረ ስለሆነ ብሔራዊ መታወቂያ ከኢት-ስዊች ጋር በመቀናጀት ሁሉንም ባንኮች በአንድ ጊዜ ማግኘት ይችላል።
የባንክ አካውንት ሲከፈት ባንኮች የብሔራዊ መታወቂያ ቁጥሩን ወደ ኢትስዊች ልከው ኢት-ስዊች ባንኩ ስለደንበኛው የሚያስፈልገውን መረጃ (KYC) ከብሔራዊ መታወቂያ ተቀብሎ ለባንኮቹ መልሶ ይልካል።
የብሔራዊ መታወቂያ የጣት አሻራን በክፍያ ወቅት እንደ ይለፍ ቃልም መጠቀም እንዲቻል አሁን ላይ የተጀመሩት ትስስሮች እንደሚያግዙም ተጠቅሷል።
ኢት-ስዊች የፋይናንስ ሪፖርቱን በቅርቡ ሲያቀርብ በባለፈው በጀት ዓመት ጠቅላላ ገቢው 2.2 ቢሊዮን ብር መሆኑን ጠቅሶ ከታክስ በፊት 1.42 ቢሊዮን ብር ማትረፉንና ይህም ካለፈው የበጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ34% ጭማሪ ማሳየቱን ገልጿል።
ኢትዮጵያ በድጅታል ኢትዮጵያ 2025 እቅድ መሰረት ብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባን ወደ 70 ሚሊዮን ለማድረስ እቅድ ማስቀመጧ ይታወሳል፡፡
የቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ድጅታል ኢትዮያ 2030 እቅድ በመዘጋጀት ላይ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን አሁን ላይ የብሔራዊ መታወቂያ ተመዝጋቢዎች ቁጥር 28 ሚሊዮን መድረሱን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት አስታውቋል፡፡
የብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባ ከዚህ በፊት በከተሞች ብቻ ሰጥ የነበረ ሲሆን ቀስ በቀስ ወደ ሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በመስፋፋት ላይ መሆኑን የፕሮጀክቱ ስራ አስፈጻሚ አቶ ዮዳሄ ዘሚካኤል ገልጸዋል፡፡
የብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባ በተመረጡ የመንግስት ተቋማት፣ በባንክ ቅርጫፍ ቢሮዎች፣ እንደ ኢትዮ ቴሌኮም እና መሰል አገልግሎት መስጫ ቦታዎች እየተካሄደም ይገኛል፡፡
ተጨማሪ የብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባ ለማካሄድም ለግል የቴክኖሎጂ ኩባያዎች ማስታወቂያ ወጥቷል፡፡
አሁን ላይ የብሔራዊ መታወቂያ ለበርካታ የመንግስት አገልግሎቶች እንደግዴታ የተቀመጠ ሲሆን የሚመዘገቡ ዜጎችም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል፡፡