ብሔራዊ ባንክ አስመጪዎች እና ላኪዎች ያለ ባንክ ቅድመ እውቅና እቃ እንዲያዙ ፈቀደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወደ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ሥርዓት እያደረገ ያለውን ሽግግር ለማጠናከር፣ የውጭ ምንዛሬ አስተዳደርን የሚያቀሉ አዳዲስ መመሪያዎችን ይፋ አድርጓል።

ባንኩ ባወጣው መግለጫ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሬ አስተዳደርን ይበልጥ ለማቅለልና በንግድ እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት የሆኑ የቢሮክራሲ ሰንሰለቶችን የሚያሳጥሩ ናቸው።

በአዲሱ መመሪያ መሰረት የንግድ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ ሂሳብ እና የውጭ ምንዛሬ ተመላሽ ሂሳብ  ላላቸው ደንበኞች የብድር ደብዳቤ እና የሰነድ መክፈያ ፈቃዶችን ያለ ብሔራዊ ባንክ ቅድመ ሁኔታ ማጽደቅ እንዲችሉ ሙሉ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል።

ይህ ማሻሻያ በተለይ በገቢና ወጪ ንግድ ላይ ለተሰማሩ ነጋዴዎች የጊዜና የቢሮክራሲ ጫናን ያቀላል ተብሎ ይጠበቃል።

በተጨማሪም የውጭ ምንዛሬ ሂሳብ ያላቸው ተቋማት የባንኮችን ቅድመ ፈቃድ ሳይጠብቁ በሰነድ መክፈያ ስምምነት መሠረት የሸቀጦችን የጭነት ትዕዛዝ መስጠት ወይም ጭነት ማስጀመር እንዲችሉ ፈቅዷል።

እንደ ብሔራዊ ባንክ አዲስ መመሪያ ከሆነ የክፍያ ሂደቱ የሚፈጸመው አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶች ቀርበው ሲረጋገጡ ብቻ ነው።

ባንኩ በንግድ ባንኮች የሚጠየቁ የብድር ደብዳቤ (LC) የአገልግሎት ክፍያዎችና ኮሚሽኖች ከዓለም አቀፍ አሰራር ጋር የማይጣጣሙ ሆነው ማግኘቱን ጠቁሟል።

ይህንን ለማስተካከልም ከአሁን በኋላ ባንኮች የሚጠይቁት የአገልግሎት ክፍያ በዓመታዊ ስሌት ተሰልቶ፣ እንደ ሰነዱ ቆይታ ጊዜ ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ እንዲቀነስ አዟል።

በተጨማሪም ባንኮች የሚጥሉት ዓመታዊ የክፍያ መጠን ብሔራዊ ባንክ ቀደም ብሎ ካስቀመጠው ከፍተኛ የክፍያ ጣሪያ መብለጥ እንደሌለበት በመመሪያው በጥብቅ አሳስቧል።

ባንኩ በኢትዮጵያ የተረጋጋና ውጤታማ የውጭ ምንዛሬ ግብይት እንዲኖር ተጨማሪ እርምጃዎችን እንደሚወስድ ገልጿል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *