ኡሁሩ ኬንያታ በኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድንን እንዲመሩ ተመረጡ

የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ 73 አባላትን ያቀፈ የአፍሪካ ኅብረት ግንቦት 24 ቀን 2018 በሚካሄደው የኢትዮጵያ ምርጫ 2018 ታዛቢ ልዑካን ቡድን ይመራሉ ተብሏል።

በቀድሞው የኬኒያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚመራው፣ የአፍሪካ ኅብረት የታዛቢዎች ልዑካን ቡድን አዲስ አበባ መግባቱን ኅብረቱ አስታውቋል።

ታዛቢ ቡድኑ ከ37 አገራት የተውጣጡ 73 አባላትን ያቀፈ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ ከታዛቢዎቹ ውስጥ 61 በመቶዎቹ ሴቶች እንደሆኑ ተገልጿል።

የአፍሪካ ኅብረት የታዛቢዎች ቡድን የሚሰማራው ለአጭር ጊዜ ታዛቢነት ሲሆን፣ ጊዜያዊ ጽ/ቤቱን በስካይላይት ሆቴል እንደሚያደርግ አሳውቋል።

ታዛቢዎቹ በሁሉም ምርጫ የሚካሄድባቸው አካባቢዎች እንደሚሰማሩም ተገልጿል።

ሰባተኛውን አጠቃላይ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅቴን ጨርሻለሁ ያለው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአማራ ክልል በ8 የምርጫ ክልሎች ሊካሄድ የታሰበው ምርጫ መራዘሙን አስታውቋል።

ቦርዱ የቅድመ ምርጫ አጠቃላይ እንቅስቃሴዎችን በተመለከ ግንቦት 18 ቀን 2018 ዓ.ም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በአማራ ክልል በስምንት የምርጫ ክልሎች ምርጫ እንደማይካሄድ የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ በመጪው ሰኞ፣ ግንቦት 24፣ 2018 ምርጫው በእነዚህ የምርጫ ክልሎች አይካሄድም ማለት፣ ሌላ ጊዜ አይካሄድም ማለት አይደለም ሲሉ ሰብሳቢዋ አክለው ተናግረዋል።

በአማራ ክልል 138 የምርጫ ክልሎች ያሉ ሲሆን፣ በሁሉም የምርጫ ክልሎች ተወዳዳሪ ዕጩዎች መመዝገባቸውን የቦርዱ መረጃ ያመላክታል።

በክልሉ፣ ለፓርላማ ከሚወዳደሩ ዕጩዎች መካከል 11ዱ ያለምንም ተፎካካሪ ተመዝግበዋል።

ቦርዱ በመግለጫው ምርጫ እንደማይካሄድባቸው የገለጻቸው ስምንት የምርጫ ክልሎች እነማን እንደሆኑ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።

42 የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚወዳደሩበት የዘንድሮው ሀገር አቀፍ ምርጫ ዝቅተኛ ፉክክር ታይቶበታል።

በአማራ፣ ኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ያለው የጸጥታ ችግር በምርጫው ላይ ስጋቶችን ሲደቅን በትግራይ ክልል ደግሞ ምርጫው አይካሄድም ተብሏል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *