የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኅብረት እንደገለጸው ምልከታ ካደረገባቸው 2 ሺህ 258 ምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ በ947 ወይም 42 በመቶዎቹ ላይ ከንጋቱ 12 ሰዓት በፊት ድምጽ መሰጠት መጀመሩን ማረጋገጡን ገልጿል፡፡
ድርጅቱ ዛሬ ግንቦት 24፣ 2018 በመካሄድ ላይ ባለው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫን አስመልክቶ ምልከታ ባደረገባቸው የምርጫ ጣቢያዎች የተስተዋሉ ክስተቶችን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የኅብረቱ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሳህለሥላሴ አበበ በመግለጫው ላይ እንዳሉት ከትግራይ ክልል ውጪ በቀሪዎቹ ሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተካሄደ ባለው ምርጫ የግማሽ ቀን ምልከታ ሪፖርት ይፋ አድርገዋል፡፡ በዚህም የህብረቱ ታዛቢዎች ከተገኙባቸው 2 ሺህ 258 ምርጫ ጣቢያዎች መካከል በ1 ሺህ 276 ወይም 57 በመቶዎቹ ከንጋቱ 12 ሰዓት እስከ 1 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ድምጽ መሰጠት ተጀምሮባቸዋል፡፡ በተቃራኒው በ31 ምርጫ ጣቢያዎች ደግሞ ድምጽ መሰጠት የተጀመረው ከአንድ ሰዓት በኋላ መሆኑን ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡ በሶስት ምርጫ ጣቢያዎች ደግሞ ሪፖርቱ እስከተጠናቀረበት ከቀኑ ሰባት ሰዓት ድረስ ድምጽ መስጠት አልተጀመረም፡፡
ሰብሳቢው አክለውም የህብረቱ ተወካዮች ምልከታ ካካሄዱባቸው ምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ 76ቱ ምርጫ ጣቢያዎች በህግ በተከለከለ ቦታ መቋቋማቸውን ጠቅሰዋል፡፡ እንዲሁም በ87 ምርጫ ጣቢያዎች በህግ የተከለከሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅስቀሳ ምልክቶች መታየጣቸው ተገልጿል፡፡
የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች የተቋቋሙበት ስፍራ ለሴቶች አመቺነትን በሚመለከት 101 ምርጫ ጣቢያዎች አመቺ አለመሆናቸው በህብረቱ ታዛቢዎች መረጋገጡን ሲገለጽ 148 ምርጫ ጣቢያዎች ደግሞ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዳልሆኑ ህብረቱ አስታውቋል፡፡
የድምጽ መስጫ ሳጥኖች ከመታሸጋቸው በፊት ባዶ መሆናቸውን ከማረጋገጥ አንጻርም ክፍተቶች መኖራቸውን ታዝበናል ያሉት የህብረቱ ሰብሳቢ አቶ ሳህለስላሴ አበበ ምልከታ ከተካሄደባቸው 2 ሺህ 58 ምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ በ26ቱ የድምጽ መስጫ ሳጥኑ ከመታሸጉ በፊት ባዶ መሆናቸው በግልጽ አለመታየታቸውን ተናግረዋል፡፡
ህብረቱ በምልከታ ሪፖርቱ ላይ 203 ክስተቶችን “አሳሳቢ” በሚል ከለያቸው ጉዳዮች መካከል 40 ይህሉ ሲረጋገጡ ቀሪዎቹን ለማረጋገጥ በሂደት ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ምርጫ ጣቢያዎችን በህክምና ተቋማት ውስጥ ማቋቋም፣ ምርጫ ጣቢያዎች ባሉባቸው በ200 ሜትር ራዲየስ ውስጥ ምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ፣ የድምጽ መስጫ ወረቀቶችን ማህተም ሳያደርጉ ማደል፣ የጸጥታ መደፍረስ፣ ያልተፈቀደላቸው ሰዎች በድምጽ መስጫ ጣቢያዎች መገኘት፣ ታዛቢዎች ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እንዳይገቡ መከልከል እና ከምርጫ አስፈጻሚዎች ውጪ የሆኑ ሰዎች መራጮችን ማገዝ በህብረቱ አሳሳቢ በሚል ከተለዩ ክስተቶች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ፣ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 4 የብልፅግና ፓርቲ አባል በምርጫው ጣብያው ውስጥ የምርጫ ቅስቀሳ ሲያከናውን መገኘቱን ህብረቱ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል፡፡
ኅብረቱ 2 ሺሕ 255 ተቀማጭ ታዛቢዎች እንዲሁም 801 ተንቀሳቃሽ በድምሩ 3 ሺሕ 149 አጠቃላይ ታዛቢዎች ማሰማራቱን ሰብሳቢው ገልጸዋል። በመግለጫው ላይ ከትግራይ ክልል 32 ምርጫ ክልሎች፣ በአማራ 8 የምርጫ ክልሎች እና አከራካሪ ከተባሉ አካባቢዎች ውጪ ኅብረቱ በሁሉም አካባቢዎች በሚገኙ 2 ሺሕ 258 የምርጫ ጣቢያዎች ታዛቢዎች ማሰማራቱ ገልጿል።
ከጸጥታ መደፍረስ ጋር በተገናኘ በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ወገራ ወረዳ አምባጊዮርጊስ ከተማ ምርጫ ጣቢያ (ቀበሌ 2) ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ድምፅ መስጠት ቢጀመርም፣ ከረፋዱ 5፡10 ጀምሮ በጣቢያው አቅራቢያ በተሰማ ተኩስ ምክንያት ሂደቱ ተቋርጧል።
በተመሳሳይ በሰሜን ወሎ መቄት በፀጥታ ምክንያት ተቆርጦ ከ1 ሰዓት በኃላ የምርጫ ሂደቱ መቀጠሉ ሲገለጽ በደቡብ ጎንደር ዞን ፋርጣ ወረዳ በተኩስ ድምጽ ምክንያት ሂደቱ ሲቋረጥ፣ በፎገራ ወረታ ከተማ ደበረ ታቦር ከተማ ቀበሌ 4 ጣቢያዎችም በተመሳሳይ ምክንያት አስፈጻሚዎች ጣቢያዎቹን ዘግተው ለመውጣት መገደዳቸው ተገልጿል።
በደብረ ታቦር ያለው ጣቢያ ረፋድ 3፡00 ሰዓት ድጋሚ ስራ የጀመረ ሲሆን፣ በእናቲቱ ማርያም ጣቢያ ደግሞ በ2፡35 በተከፈተ ተኩስ ሰራተኞች ብረት ጭነው በመውጣታቸው ሂደቱ ተቋርጧል። ሪፖርቱ አስር አማላካቾችን የየያዘ ሲሆን የመጀመሪያው ታዛቢዎች ወደ ድምፅ መስጫ ጣብያ እንዲገቡ መደረጉ በተመለከተ ከ99 በመቶ ያለምንም ገደብ መግባታቸውን ተገልጿል። ይሁን እንጂ 17 ምርጫ ጣብያዎች ታዛቢዎች ወደ ምርጫ ጣብያ እንዳይገቡ ተከልክለዋል።