የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እንዳስታወቀው ከሰኔ 17 ቀን 2018 ጀምሮ ደግሞ የግዳጅ ውትድርና ህግ ወጥቶለት ስራ ላይ መዋሉን ገልጿል።
ይህ አዋጅ የዜጎችን ሰብአዊ መብቶችን የሚጥስ በመሆኑ እንዲቆም ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡
በትግራይ ክልል የግዳጅ ውትድርና ሰነድ ከመውጣቱ አስቀድሞ በተለያዩ አካባቢዎች ወጣቶችን በተለይም ሕጻናትን፣ ተፈናቃዮችን፣ የአእምሮ ጤና ሕሙማንን፣ እንዲሁም ከስደተኛ ካምፖችና ከጸበል ሥፍራዎች ጭምር በግዳጅ በማሰባሰብ ወደ ወታደራዊ ሥልጠና ካምፖች የማስገባት ተግባር ሲፈጸም እንደነበር ኢሰመኮ ተናግሯል፡፡
ኮሚሽኑ የግዳጅ ውትድርና ሰነዱ ከወጣ በኋላም ይህ ተግባር ይበልጥ ተጠናክሮ ቀጥሎ የአብነት ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ከአብያተ ክርስትያናት፣ እንዲሁም በርካታ ሌሎች ሰዎችን ከገበያ ስፍራ፣ ከወጣቶች ማዘውተሪያ ማዕከላት እና ቤት ለቤት በሚደረግ አሰሳ በማፈስ ወደ ወታደራዊ ተግባር እንዲሰማሩ መደረጉን እና መቀጠሉን ታፍሰው ከተመለሱ ወጣቶች፣ ከቤተሰቦቻቸው እና ከተለያዩ ሰነዶች ባሰባሰበው መረጃ ማረጋገጡንም አስታውቋል።
በግዳጅ ከሚታፈሱ ሰዎች መካከልም በአብዛኛው እድሜያችዉ ከ18 ዓመት በታች መሆናቸዉን ኢሰመኮ ባደረገው ምርመራ ማረጋገጡን በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
ኮሚሽኑ ባደረገው ክትትል ክልሉ “የትግራይ ሕዝብን ሕልውና ለመጠበቅ” በሚል ወጣቶችን በግዳጅ ወደ ውትድርና የማሰማራት የውሳኔ ሰነድ ወይም ሕግ ማውጣቱንና ሥራ ላይ ማዋሉን ተመልክቻለው ብሏል።
ከሰኔ 17 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ተፈጻሚ መደረግ ጀምሯል የተባለው ይህ የግዳጅ ውትድርና ሰነድ የክልሉ ተወላጅ የሆነ ማንኛውም ሰው ለግዳጅ ውትድርና የሚቀርብለትን ጥሪ የመቀበል ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል።
ይህን “የትግራይ ህልውና ለመጠበቅ” በሚል የደረገውን ጥሪ የማይቀበል ሰው ከ10 ሺህ እስከ 50 ሺህ ብር እንደሚቀጣ በሰነዱ ላይ ተጠቅሷል።
በተጨማሪም በክልሉ ውስጥም ሆነ ከክልሉ ውጪ ሆነው ሕዝቡ ድርጊቶቹን እንዳይደግፍ የሚያደርጉ ተግባራትን የሚፈጽሙ ወይም በክልሉ የተላለፉ ውሳኔዎችን የሚተቹ ወይም የሚቃወሙ ግለሰቦች ወደ ኃላ ጭምር በመመለስ ከ5 እስከ 25 ዓመት ጽኑ እስራት እና በንብረት መወረስ እንደሚቀጡ በሰነዱ ተቀምጧል።
የጸጥታ አካላት ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማንኛውም ጊዜና ቦታ ግለሰቦችን እንዲይዙና ፍተሻ እንዲያካሂዱ ሥልጣን የሚሰጥ ድንጋጌንም ያካተተ መሆኑን ኢሰመኮ አስታውቃል።
የውሳኔ ሰነዱ የወጣው በ2012 ዓ.ም. ምርጫን ለማካሄድ ሕገ መንግስታዊ ተቋም ከሆነው የምርጫ ቦርድ እውቅና ውጪ በክልሉ ተደርጎ በነበረው ምርጫ መሠረት የተቋቋመ እንደሆነ እና በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት የፈረሰ የምክር ቤት አባላት በድጋሚ በመሰብሰብ ላይ መሆኑም ተገልጿል።
ከሰሞኑ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎች ጉዳዩ ያሳሰባቸው ሀገራት እና ተቋማት በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ስጋታቸውን እየገለጹ ሲሆን የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት እንዲከበር አሳስበዋል።