ኢትዮጵያ በአዲስ የብድር ስምምነት ዙሪያ እንድትጠነቀቅ የዓለም ባንክ አሳሰበ

ለኢትዮጵያ ተጨማሪ ከ460 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብድር ያፀደቀው የአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ከአዳዲስ የብድር ጫና እንድትቆጠብ አስጠንቅቋል፡፡

ኢትዮጵያ ከእዳ ጫና እንድትላቀቅ በምትፈጽማቸው አዳዲስ የብድር ስምምነቶች ዙሪያ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ልትወስድ እንደሚገባ አስታውቋል።

ተቋሙ አምስተኛውን የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ግምገማ ማጠናቀቁን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ተጨማሪ 464 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለኢትዮጵያ አጽድቋል።

የተቋሙ የበጀት ድጋፍ ከሁለት አመት በፊት ያፀደቀውና ለአራት አመት በሂደት የሚለቀቅ በሚል የፈቀደው የ3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ብድር አካል ነው፡፡

የአይኤምኤፍ የስራ አመራር ቦርድ ያፀደቀው የ464 ሚሊዮን ዶላር ብድር እስካሁን በአራት ዙር ከተለቀቀው ሁሉ የላቀ ሲሆን ለወደፊቱ ከሚለቀቀው ብድር ታሳቢ የሚደረግ የ200 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ገንዘብ ታክሎበታል።

ጭማሪ ገንዘቡ ለኢትዮጵያ የተለቀቀው የኢራን ጦርነት የፈጠረባትን ጫና ለማቃለል እንዲያግዛት ታስቦ እንደሆነም ተገልጿል።

እስካሁን ድረስ ጠንካራ የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ቢስተዋልም የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ጫና መፍጠሩ በተቋሙ መግለጫ ተጠቅሷል፡፡

በመሆኑም በተለይም የነዳጅ ዋጋ በአለም አቀፍ ደረጃም ከፍተኛ ጭማሪ በማሳየቱ እና ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ከውጭ በሚገባ ነዳጅ ላይ ጥገኛ በመሆኗ በአምስተኛው ዙር ግምገማ አይኤምኤፍ ተጨማሪ የ200 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ በመፍቀድ 464 ሚሊዮን ብድር እንዲፈቀድ ወስኗል፡፡

የአሁኑ ገንዘብ ኢትዮጵያ እስካሁን ከተቋሙ የወሰደችውን ብድር 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር አድርሶታል፡፡

በተጨማሪም ከአይኤምኤፍ ጋር የተደረገውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ የኢትዮጵያ የበጀት ጉድለቷን ለመሙላት ከብሔራዊ ባንክ ብድር መውሰድ ወይም የገንዘብ ማተም ማቆሟን የብሔራዊ ባንክ ገዚው ዶክተር እዮብ ማሞ ተናግረዋል፡፡

በአምስተኛው ዙር የአይኤምኤፍ ግምገማ ኢትዮጵያ የገቢ ግብር አሰባሰቧን በማሳደጓ ፣ የውጭ ምንዛሬ አሰራርንም አሻሽላለች ተብሏል፡፡

ያለባትን የውጭ እዳ ለማሸጋሸግ ከአበዳሪዎቿ ጋር የሁለትዮሽ ስምምነቶችን መፈራረሟ እና ከአለም አቀፍ የንግድ አበዳሪዎቿ ጋርም የምታደርገው ድርድር መሻሻል ማሳየቱን በበጎ እንደሚመለከተውም ተቃሙ አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም ከዩሮ ቦንድ አበዳሪዎቿ ጋር በመርህ ደረጃ ስምምት ላይ መድረሷንም አይኤምኤፍ እንደተቀበለው በመግለጫው ላይ ጠቅሷል፡፡

በሌላ በኩል ግን የስራ አስፈፃሚ ቦርዱ ኢትዮጵያ ተጨማሪ አዳዲስ ብድሮችን በመውሰድ ረገድ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስቧል፡፡

ከሰሞኑ ኢትዮጵያ ከጣልያን መንግሥት ጋር ለአካባቢ ጥበቃ፣ ዘላቂ ልማት እና ሌሎች ስራዎች የ80 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ስምምነት መፈራረሟ ይታወሳል።

የዓለም ባንክ ከሁለት ሳምንት በፊት ኢትዮጵያ የጀመረችው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማስፈጸሚያ የ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የበጀት ድጋፍ ለማድረግ መስማማቱ አይዘነጋም።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *