የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የሀገሪቱ ዋነኛ የወጪ ንግድ ገቢ ምንጭ በሆነው የቡና ምርት ላይ የሚፈጸመውን ህገ-ወጥ ዝውውር (ኮንትሮባንድ) ለመግታት፣ ከተባባሪ አካላት ጋር በመቀናጀት ጥብቅ የሆኑ የቁጥጥርና የቅጣት እርምጃዎችን መተግበር መጀመሩን አስታውቋል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶ/ር ሰፊሳ አባቡ እንደተናገሩት ህገ-ወጥ የቡና ንግድ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ገቢ በእጅጉ እየጎዳ በመሆኑ፣ ድርጊቱን ለመከላከል አዲስ የክትትል ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።
በዚህም መሠረት ባለስልጣኑ ህገ-ወጥ የቡና ዝውውርን ለማስቆም ከፌዴራልና ክልል ፖሊስ፣ ከጉምሩክ ባለስልጣን እና ከገቢዎች ሚኒስቴር ጋር የጋራ ግብረ-ኃይል አቋቁሞ እየተሰራ መሆኑንም ኋላፊው አክለዋል።
በመሆኑም ያለ ህጋዊ ፈቃድና ሰነድ ሲንቀሳቀስ የተገኘ ማንኛውም የቡና ምርት ሙሉ በሙሉ በመንግስት ይወረሳል ተብሏል።
በህገ-ወጥ የቡና ንግድ ሰንሰለት ውስጥ ተሳትፈው በሚገኙ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይም እንደ ጥፋታቸው ደረጃ እስከ 50 ሚሊዮን ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት መጣሉ ተገልጿል።
የኬላዎችቁጥጥርን በተመለከተም በመረጃዎችን በፈጣን ቴክኖሎጂ በመለዋወጥ፣ በዋና ዋና የቡና አምራች ክልሎችና መውጫ ኬላዎች ላይ ፍተሻዎች ተጠናክረዋል ሲሉም ዶ/ር ሰፊሳ አክለዋል::
የኮንትሮባንድ ቁጥጥሩ ውጤታማ የሚሆነው ከመነሻው ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለገበያ ማቅረብ ሲቻል ነው” ያሉት ኃላፊው፣ ምርቱ መሬት ላይ እንዳይሰጣ እና በአልጋ ላይ እንዲደርቅ የማስተማርና የመደገፍ ስራ እየተሰራ መሆኑን ኋላፊው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ሊጠናቀቅ አንድ ወር በቀረው የዘንድሮው በጀት ዓመት ውስጥ ከቡና ንግድ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዳለች።
ባለስልጣኑ ከዚህ በፊት የዓለም ቡና ዋጋ ቅናሽ እያሳየ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ቡና ላኪዎች ምርቶቻቸውን በፍጥነት ወደ ዓለም ገበያ እንዲያቀርቡ ሲያሳስብ ቆይቷል።