ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በተራዘመው የብድር አቅርቦት ፕሮግራም አምስተኛ ግምገማ ላይ በባለሙያዎች ደረጃ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀዋል።
ይህ ስምምነት በሚቀጥሉት ሳምንታት በድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሙሉ በሙሉ ሲጸድቅ፣ ኢትዮጵያ የ468 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ተጨማሪ የፋይናንስ ድጋፍ እንድታገኝ ያደርጋታል።
ይህም ሀገሪቱ በ4 ዓመታት ውስጥ ከምታገኘው የ3.4 ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ ድጋፍ ውስጥ እስካሁን የተለቀቀላትን የገንዘብ መጠን ወደ 2.65 ቢሊዮን ዶላር ከፍ የሚያደርገው ሲሆን፣ ስምምነቱ ሊደረስ የተቻለው ከአልቫሮ ፒሪስ የተመራው የድርጅቱ ልዑክ ከሚያዝያ 28 እስከ ግንቦት 12 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ባደረገው የሁለት ሳምንታት ጉብኝትና ተከታታይ የሥራ ውይይቶች ማጠናቀቂያ ላይ ነው።
በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት መግለጫ ላይ እንደተመለከተው ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከቀጠናዊ ቀውሶች ጋር ተያይዞ የመጣውን ትልቅ ውጫዊ ጫና በመቋቋም ረገድ ከፍተኛ ጥንካሬ አሳይቷል።
ይሁን እንጂ፣ ዓለም አቀፋዊ አለመረጋጋትና የሸቀጦች ዋጋ መዋዠቅ አሁንም እያደገ በመምጣቱ በኢኮኖሚው የወደፊት ጉዞ ላይ የሚታዩት ስጋቶች መጨመራቸውን አይ ኤም ኤፍ አስጠንቅቋል።
የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መረጋጋት በዘላቂነት ለማስቀጠልም ድርጅቱ ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ቁልፍ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን የጠቆመ ሲሆን፣ ይህም የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲን አጠናክሮ መቀጠልን፣ የውጭ ምንዛሬ ገበያውን ግልጽነትና አሠራር ይበልጥ ማሻሻልን እንዲሁም የአገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብን በማጠናከር የወጪ አያያዝን በጥንቃቄ መምራት አስፈላጊ መሆኑን አሳስቧል።
ይህ በዚህ እንዳለ አይኤምኤፍ የኢትዮጵያ መንግሥት ብር ከሌሎች የውጭ ሀገራት መገበያያ ገንዘቦች ጋር ያለውን ልዩነት እንዲያሰፋ፣ የድጎማ በጀቶችን ሙሉ ለሙሉ እንዲያቆም እና አዳዲስ የግብር መሰብሰቢያ አማራጮችን እንዲያሰፋ በምክረ ሀሳብ ደረጃ ማቅረቡ ተሰምቷል።
የድርጅቱ ማሳሰቢያዎች በርካታ ኢትዮጵያውያን በስጋትነት የተመለከቱት ሲሆን በተለይም የኑሮ ውድነቱን እንደሚያባብሰው እየገለጹ ይገኛሉ።