ዋና መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው አምንስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ በተለይም በአማራ ክልል ዋና ዋና ከተሞች አዲስ እስር እየተካሄደ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
ከመስከረም 18 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የመንገስት የጸጥታ ሀይሎች ዜጎችን ከህግ ውጪ እየያዙ እያሰሩ መሆኑንም ተቋሙ በሪፖርቱ ለይ ጠቅሷል፡፡
በአምንስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ዳይሬክተር ትግሬ ቻጉታህ እንዳሉት “የኢትዮጵያ የጸጥታ ሀይሎች ንጹሃንን ከህግ ውጪ በዘመቻ ማሰር መጀመራቸው መንግስት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ፍላጎት እንደሌለው ማሳያ ነው” ብለዋል፡፡
ተቋሙ የአይን እማኞችን ጠቅሶ ባወጣው በዚህ ሪፖርቱ ላይ እንደገለጸው ለእስር የተዳረጉ ንጹሃን ህጉ በሚፈቅደው መሰረት በ48 ሰዓት ውስጥ ወደ ፍርድ ቤት እየቀረቡ አለመሆኑንም አስታውቋል፡፡
መንግስት ጀመረው በተባለው የዘመቻ እስር በክልሉ ባሉ ከተሞች የሚገኙ መምህራን እና ሌሎችም የማህበረሰብ ክፍሎች ኢላማ እንደተደረጉም ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ከሀገሪቱ ህገ መንገስት ውጪ ለእስር የተዳረጉ እና መብታቸው የተገፈፉ ሰዎችን ከእስር እንዲለቁም አምንስቲ አሳስቧል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ካሳለፍነው ሰኔ ወር ጀምሮ በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርቱን ባሳለፍነው ሳምንት ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡
ኢሰመኮ በዚህ የአራት ወራት ሪፖርቱ በአማራ ክልል በመንግስት እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ባለው ግጭት ከ160 በላይ ንጹሃን መገደላቸውን አስታውቋል፡፡
ከአማራ ክልል በተጨማሪም በኦሮሚያ፣ ጋምቤላ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በተመሳሳይ በርካታ ንጹሃን መገደላቸውን ገልጾ በመንግስት እና ታጣቂዎች መካከል እየተካሄዱ ያሉ ግጭቶች እንዲቆሙ ማሳሰቡም ይታወሳል፡፡
የአማራ ክልል መንግስት ኮሙንኬሽን በበኩሉ በክልሉ ያለውን የጸጥታ ችግር በውይይት ለመፍታት ቢሞክርም ምላሹ ሌላ በመሆኑ መንግስት ህግ እንደሚያስከብር አስታውቋል፡፡
የሀገር መከላከያ ሰራዊት ህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ኮለኔል ጌትነት አዳነ በበኩላቸው በአማራ ክልል የተጀመረው ህግ የማስከበር ስራ የሚቆመው በክልሉ ሰላም ከሰፈነ ብቻ ነው ብለዋል፡፡