የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተጓደሉ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የቀረቡ አራት ዕጩዎችን ሹመት አጽድቋል።
ዶ/ር ሚዛኔ አንጋፋ የሰብአዊ መብቶች ምሁር እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብአዊ መብቶች ሕግ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆኑ፤ በሰብአዊ መብቶች ክትትል፣ በተቋማዊ ሪፎርም እና በሕግ ትምህርት ረገድ ሰፊ ልምድ አላቸው።
በኢሰመኮ ውስጥ በተለያዩ ከፍተኛ የአመራር ኃላፊነቶች ያገለገሉ ሲሆን፣ በቅርቡም የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ በመሆን በፖሊሲ ልማት እና በተቋማዊ ግንባታ ረገድ ጉልህ አስተዋጽዖ አበርክተዋል።
አቶ በዳሳ ለሜሳ ከበደ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት እና ሥልጠና ኮሚሽነር በመሆን ተሹመዋል።
አቶ በዳሳ በሰብአዊ መብቶች ክትትል፣ በምርመራ እና በተቋማዊ አመራር ሰፊ ልምድ ያላቸው አንጋፋ ባለሙያ መሆቸው ተገልጿል።
በቅርቡ በኢሰመኮ የክትትል እና ምርመራ ከፍተኛ ዳይሬክተር በመሆን ያገለገሉ ሲሆን የሙያ ብቃታቸው የኮሚሽኑን የሥራ ክንውን እና የአሠራር ሥርዓቶችን በማጠናከር ረገድ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።
አቶ መሐመድ አሕመድ ሐሰን የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር በመሆን ተሹመዋል።
በፍትሕ እና በሰብአዊ መብቶች ዘርፎች ከ18 ዓመታት በላይ የካበተ ልምድ ያላቸው ሲሆን በኮሚሽኑ የስብአዊ መብቶች ሪጅናል ዳይሬክተር፣ በአፋር ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዳኝነት ከማገልገላቸውም በላይ፤ በፍትሕ ሥርዓት፣ በሰብአዊ መብቶች ጥበቃ እና በተቋማዊ ሪፎርም ረገድ ያላቸውን ጥልቅ ዕውቀት እና ተሞክሮ ወደ አዲሱ ኃላፊነታቸው ይዘው መጥተዋል።
ኢሰመኮ በተመሳሳይ መልኩ ወይዘሮ አሸነፈች አበበ አልቢን የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር በመሆን መሾማቸውን አስታውቋል።
ከፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንትነት የመጡት ወይዘሮ አሸነፈች፤ በዳኝነት፣ በዐቃቤ ሕግነት እና በሕግ ባለሙያነት ያገለገሉ አንጋፋ የፍትሕ ዘርፍ አመራር ናቸው።
በተለይም ሕፃናትን ማዕከል ያደረገ የፍትሕ ሥርዓትን በማሳደግ፣ የሕፃናት ተስማሚ ችሎቶችን በማቋቋም እና የሴቶችንና የሕፃናትን መብቶች በማስከበር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።