ምርጫ ቦርድ 22 ምርጫ ጣቢያዎች መዘጋታቸውን ገለጸ

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮችን ምዝገባ እንዲያከናውኑ ከተከፈቱ ምርጫ ጣቢያዎች መካከል 22ቱ ህገወጥ ድርጊት በመፈጸማቸው ምክንያት መዘጋታቸውን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

ለ45 ቀናት ሲካሄድ የነበረው የመራጮች ምዝገባ መጠናቀቁን አስመልክቶ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሜላትወርቅ ሀይሉ በሰጡት መግለጫ የመራጮች ምዝገባ 50 ሚሊዮን ማለፉን ተናግረዋል፡፡

የተዘጉት የምርጫ ጣቢያዎች ተመሳሳይ መራጭ በተለያዩ የምርጫ ጣቢያ ላይ ተመሳሳይ ፊርማ የተገኙባቸውም አሉ ብሏል።  ቦርዱ መስራት የሚጠበቅባቸውን ስራ ወደ ጎን በመተው ህግን ያላከበረ አሰራር መከተላቸውንም አመልክቷል።

በተመሳሳይ እንዲህ ዓይነት ድርጊት ላይ የተሳተፉ የምርጫ አስፈፃሚዎችም ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል።

ቦርዱ እርምጃ እንደወሰደ ቢገልጽም በምን ያህሎቹ ላይ እንደወሰደ ግን ያለው ነገር የለም።  ቦርዱ ከዚህ ቀደም በደመወዝ እና በተለያዩ ጉዳዮች በማስፈራራት ዜጎች በግዴታ ካርድ እንዲወስዱ እየተደረጉ መሆኑን ገልፆ ነበር።

የተዘጉት ጣቢያዎችም በኦሮሚያ 12፣ በሶማሊ 6፣ በሲዳማ ክልል 2፣ በአማራ 1 እና ሐረሪ ክልል 1 መሆናቸውን ሰብሳቢዋ ሜላተወርቅ ኃይሉ ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሰሩ ሠራተኞች ምርጫ ካርዱን ከወሰዱ በኋላ፣ ፎቶግራፍ አንስተው እንዲልኩ መገደዳቸውን የገለጸው ቦርዱ ይህም የህግ ጥሰት መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡

ቦርዱ በዚሁ መግለጫው ፓርቲዎች እስከ ሚያዝያ 23 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ እጩዎቻቸውን መቀየር እና መተካካት ይችላሉ ያለ ሲሆን ከዚያን ዕለት ጀምሮ የመጨረሻዎቹን እጩዎች እንደሚያሳውቅ ገልጿል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባ መጠናቀቁን አስመልክቶ የመራጮችን ቀጥር ይፋ ያደረገ ሲሆን መከላከያ ሰራዊትን፤ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን እና የሀገር ውሰጥ ተፈናቃዮችን ሳይጨምር 50 ነጥብ 5 ሚሊዮን መራጮች ተመዝግበዋል ተብሏል።

ከዚህ ውስጥ ከ45 ሚሊዮን በላይ በማንዋል፣ አምስት ሚሊዮን በላይ ደግሞ በድጅታል በኩል እንደተመዘገቡ ቦርዱ ገልጿል። 

በዓለምአቀፍ እና ሃገር ውስጥ ባለው ሁኔታ የአገልግሎትን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮች ዋጋ በመናሩ ምክንያት ቦርዱ የበጀት ጭማሪ ጥያቄ ማቅረቡን የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ተናግረዋል።

ከ76 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ምርጫ አስፈፃሚዎች ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ክፍያ መፈጸሙን የገለጸው ቦርዱ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ከ81 ሚሊዮን በላይ ብር ወጪ ማድረጉንም ሰብሳቢዋ ገልጸዋል።

ሰባተኛው ሀገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ ከአንድ ወር በኋላ ይካሄዳል የተባለ ሲሆን ግንቦት 24 የድምጽ መስጫ ቀን ሲሆን ሰኔ 10 ደግሞ የምርጫ ውጤት ለህዝብ ይፋ እንደሚሆን ቦርዱ ከዚህ በፊት መናገሩ ይታወሳል፡፡ 

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *