ህወሃት ታጣቂዎቹ በሱዳን ጦርነት እየተሳተፉ ነው መባሉን አስተባበለ

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዛሬ ባወጣው መግለጫ “የህወሓት ኃይሎች” ከሱዳን ጦር ጎን በቅጥረኝነት ተሰልፈው ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጋር እየተዋጉ ነው መባሉን አስተባብሏል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይህን ያለው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች በትናትናው እለት ባወጣው መግለጫ የህወሓት ኃይሎች ከሱዳን ጦር እና ተባባሪ ሚሊሻዎች ጋር ሆነው እየተዋጉት እንደሆነ ማረጋገጡን መግለጹን ተከትሎ ነው።

የሱዳን ጦርነት ከተጀመረበት ከሚያዝያ 2023 ወዲህ የሱዳን ጦር የውጭ ቅጥረኞችን እርዳታ እየፈለገ ነው የሚል ክስ ያቀረበው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር፣ በጦርነት ወቅት ተገድለው የተገኙ ቅጥረኞችን መመዝገቡን ጠቅሷል።

የህወሓት ኃይሎች ከሱዳን ጦር ጎን ተሰልፈው  እየተዋጉ ነው የሚለውን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች “መሰረተ ቢስ ክስ” በጽኑ እንደሚያወግዝ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ገልጿል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንደገለጸው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ይህን ክስ ያቀረበው፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ያለቁበትን የእርስበርስ ጦርነት አለምአቀፋዊ ይዘት በማባባስ በሱዳን ጦር ላይ ለሚያደርገው ዘመቻ ድጋፍ ለማሰባሰብ ነው ብሏል።

ህወሓት በሱዳን ጦርነት ውስጥ እየተሳተፈ ነው የሚለው ክስ  ከፈጠራ ያለፈ አለመሆኑን የገለጸው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ ህወሓት የፖለቲካ ፓርቲ በመሆኑ ታጣቂ ክንፍ እንደሌለው በግለጽ የሚታወቅ ነው ብሏል።

በሰሜን ኢትዮጵያ፣ በፌዴራል መንግስታት እና በህወሓት መካከል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ መጠለያ ፍለጋ ወደ ሱዳን የተሰደዱ የትግራይ ተወላጆች መኖራቸውን እና በችግር ውስጥ ያለው የሱዳን መንግስትም እርዳታ እንዳደረገላቸው የጠቀሰው የጊዜያዊ አስተዳደሩ መግለጫ፣ “ትግራይ በሱዳን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የምትገባበት ምክንያት የለም” ብሏል።

በጦርነቱ ወቅት “ትግራይ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ባልሆነ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት” ከፍተኛ መከራ አስተናግዳለች፤ በሱዳን ጦርነትም የውጭ ኃይሎች ተሳትፎ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽዕኖ የትግራይ ህዝብ ይረዳል ብሏል ጊዜያዊ አስተዳደሩ።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ከግጭት አባባሽ መግለጫዎች እንዲታቀቡ እና ለግጭቱ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲሹ ጠይቋል።

የሱዳን ጦር፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር ባቀረበው ክስ ላይ ምላሽ አልሰጠም።

በሱዳን መፈንቅለ መንግስት ያደረጉት ሁለት ጀነራሎች በሚመሩት ጦር መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት በሺዎች እንዲገደሉ እና ከ6 ሚሊዮን በላይ ሱዳናውያን ወደ ግብጽ፣ ቻድ እና ኢትዮጵያ እንዲሰደዱ አድርጓቸዋል።

የአማራ ክልል ከሰሞኑ በህወሃት ታጣቂዎች ለአራታኛ ዙር ወረራ ፈጽመውብኛል የሚል መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ግን ደቡብ ትግራይ በሚለው ዞን ውስጥ ባሉ አወዛጋቢ ቦታዎች እየሆኑ ያሉ አዳዲስ ሁነቶች በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት የተደረጉ ናቸው ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

የአፍሪካ ህብረት በበኩሉ በአወዛጋቢዎቹ ራያ አላማጣ፣ ዛታ እና ኦፎላ “በአካባቢው ማህበረሰብ መካከል ያሉ ውጥረቶችን” በትኩረት እየተከታተሉት መሆኑን ገልጿል።

በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በተደረሰው የፌደራል መንግስት እና የህወሓት የዘላቂ ሰላም ስምምነት፣ ሁለቱ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱባቸው “አወዛጋቢ ቦታዎች” በህገመንግስቱ መሰረት እልባት እንዲያገኙ እንደሚደረግ ህብረቱ ጠቅሷል።

ከአፍሪካ ህብረት በተጨማሪም መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የሰባት ሀገራት ኤምባሲዎች በአማራ እና ትግራይ ከልል አዋሳኝ ቦታዎች ላይ ያጋጠመው አዲስ ግጭት እንዳሳሰባቸው አስታውቀዋል፡፡

የተመድ ሰብዓዊ መብት ድርጅት በበኩሉ በራያ እና አላማጣ አካባቢዎች በተከሰተው አዲስ ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ከ50 ሺህ ማለፉን መናገሩም አይዘነጋም፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *