ኢትዮጵያ ያቀረበችው የባህር በር ጥያቄ በጎረቤት ሀገራት ውድቅ ተደረገ

ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስት አብይ አህመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የህዝቧን የመልማት ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት የባህር በር ያስፈልጋታል ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ የጣላቁ ህዳሴ ግድብን ስትገነባ ጉዳዩ ያሳሰባቸው ሀገራት ጠይቀዋል፣ እኛም የባህር በር እንዲኖረን መጠየቅ አለብን ሲሉም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የባህር በር ያስፈልጋታል ያበሉ እንጂ ስለየትኛው የባህር በር ግን ስም አልጠቀሱም ነበር፡፡

ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ጎረቤት የሆኑት እና የባህር በር ያላቸው ኤርትራ፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ ሲሆኑ ሶስቱም ሀገራት የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ውድቅ አድርገዋል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ አስቀድሞ መግለጫ ያወጣው የኤርትራ መንግስት ሲሆን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል ባወጣው መግለጫ ሀገሪቱ ሀብቷን ለማንም አሳልፋ እንደማትሰጥ፣ እስካሁንም የተጀመረ ምንም አይነት ጥያቄ እንዳልቀረበ ገልጿል፡፡

የጅቡቲ መንግስት በበኩሉ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የባህር በር ጥያቄ እንደማትቀበለው አስታውቃለች፡፡

ሌላኛዋ የባህር በር ያላት የኢትዮጵያ ጎረቤት ሶማሊያ ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ እንደምትሰራ ገልጻ የወደብ ጉዳይን ግን እንደማትቀበለው ገልጻለች፡፡

ከሶማሊያ ውጪ ጅቡቲ እና ኤርትራ ራሳቸውን ሀገር ከመሆናቸው በፊት የኢትዮጵያ ግዛት አካል የነበሩ ሲሆን ኤርትራ በህዝበ ውሳኔ በ1987 ራሷን የቻለች ሀገር ሆናለች፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የባህር በር አጀንዳን ካነሱበት ጊዜ ጀምሮ ዋነኛ መወያያ አጀንዳ የሆነ ሲሆን አንዳንዶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወደብ ጥያቄውን ያነሱት በሀገር ውስጥ የገጠማቸውን የሕዝብ ተቃውሞ ለማርገብ ነው እያሉ ነው፡፡

ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱት ጥያቄ ለኢትዮጵያ አስፈላጊ እና ጥያቄውን የማንሳት ህጋዊ መብት አላት በሚል ደግፈዋል፡፡

ኢትዮጵያ አሰብ እና ምጽዋ ወደቦች የነበሯት ቢሆንም ኤርትራ በህዝበ ውሳኔ ከተገነጠለችበት 1985 ዓ.ም ጀምሮ ወደብ አልባ ሀገር ሆና ቆይታለች፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ በሀገር መከላከያ ስር የባህር ሀይሏን በማደራጀት ላይ ስትሆን የሰው ሀይል እና የጦር መርከቦችን እያደራጀች እንደሆነም ተገልጿል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *