በአማራ ክልል በተለይም ከአንድ ሳምንት በፊት አንስቶ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ይታወሳል፡፡
በሱዳን በተከሰተው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት የተሻለ ደህንነት ፍለጋ በሚል በተማ አድርገው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሱዳናዊያን ዜጎች ችግር ውስጥ መግባታቸውን ለአልዐይን ተናግረዋል፡፡
በተለይም በጎንደር እና በባህርዳር ባሉ ሆቴሎች የቆዩ ሱዳናዊያን በምግብ እጥረት፣ ደህንነት እና ትራንስፖርት ችግር ገጥሞናልም ብለዋል፡፡
ቁጥራቸው ከአንድ ሺህ በላይ እንደሚሆኑ የነገሩን እነዚህ ሱዳናዊያን መንገደኞች ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከዚያም ወደ ሳውዲ አረቢያ እና ሌሎች ሀገራት የመጓዝ አቅድን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡ ተናግረዋል፡፡
ሱዳናዊያኑ በተለይም ከጎንደር እና ብህርዳር ከተሞች ውስጥ ባሉ ሆቴሎች ከተጠለሉት በተጨማሪም በመተማ በኩል አድርገው ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ከገቡ በኋላ ጦርነት በመጀመሩ ለተለያዩ ችግሮች መዳረጋቸውንም አክለዋል፡፡
እኛ ስደተኞች አይደለንም የሚሉት እነዚህ ሱዳናዊያን ሱዳን ውስጥ ባለው ጦርነት ምክንያት ወደ ውጪ ሀገራት መጓዝ የሚቻለው በኢትዮጵያ ብቻ በኩል በመሆኑ እና ህጋዊ የጉዞ ሰነዶችን ይያዙ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስትም ይሁን ቀይ መስቀል የጦርነት ቀጠና ከሆነው ጎንደር እና ባህር ዳር እንዲያስወጧቸው ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል በበኩሉ በአማራ ክልል ባለው ጦርነት እና ግጭት ምክንያት የተጎዱ ዜጎችን ለመርዳት እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ እንዳለው የጦርነቱ ተሳታፊዎች ተጎጂዎች ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያገኙ እና ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ህጎችን እንዲያከብሩ ከተለዩዩ አካላት ጋር ውይይቶችን በማድረግ ላይ መሆኑንም ገልጿል፡፡
ቀይ መስቀል ማህበር በቀጣዮቹ ቀናትም ግጭቱ እና ጦርነቱ ባለባቸው አካባቢዎች እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎችን መርዳት በሚችልባቸው መንገዶች ዙሪያ መረጃዎችን ይፋ አደርጋለሁ ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡
በአማራ ክልል የተጀመረው ጦርነት እንዲቆም እና ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ የሀገር ውስጥ እና የውጭ አካላት በማሳሰብ ላይ ሲሆኑ የፌደራል መንግስትም ለድርድር ዝግ አለመሆኑን ከሰሞኑ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡