በኢትዮጵያ 10 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፍ የአሳንሰር ማምረቻ ፋብሪካ ለመገንባት የሚያስችል የጋራ ኢንቨስትመንት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስምምነት ተፈርሟል።
ስምምነቱን የተፈራረሙት ሀገር በቀሉ ሞናጎ ኢሊቬተር እና የቱርኩ ኬ አር ሲ ኢሊቬተር መሆናቸው ተገልጿል።
ሁለቱ ኩባንያዎች ላለፉት 5 ዓመታት በዘርፉ አብረው ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ በዱከም ከተማ ማምረቻ ፋብሪካ በጋራ ለመገንባት የሚያስችላቸውን ስምምነት ፈጽመዋል።
የ”ሞናጎ” ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋሁን ኢሳያስ እንዳስታወቁት፣ ፕሮጀክቱ በዋናነት በሀገሪቱ በሚገኙ ህንጻዎች ላይ የሚታየውን የአሳንሰር ጥገና እና የመለዋወጫ አቅርቦት እጥረት ለመፍታት ያለመ ነው።
በጨረታ የሚገዙ አሳንሰሮች ከሽያጭ በኋላ በቂ የጥገና አገልግሎት እና የመለዋወጫ አቅርቦት ስለማያገኙ በተደጋጋሚ ብልሽት እንደሚያጋጥማቸው ተመላክቷል።
አዲሱ ስምምነት ይህንን ክፍተት እንደሚሞላው የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ፣ ፋብሪካው የቱርኩን ኩባንያ ማሽነሪዎች እና ቴክኖሎጂ ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገባ ይሆናል ብለዋል።
በተጨማሪም ለሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት የቴክኖሎጂ ሽግግር የማድረግ እቅድ መያዙ ተገልጿል።
የጋራ ኢንቨስትመንቱ ግንባታው ተጠናቆ ምርት ማቅረብ ሲጀምር አሳንሰሮችን እና መለዋወጫዎችን ከውጭ ለማስገባት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ከማስቀረት ባለፈ በህንፃዎች ላይ የሚያጋጥሙ የአገልግሎት መቆራረጥ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያስችል ተቋሙ አስታውቋል።
በኢትዮጵያ አንድ ብቻ የሊፍት ወይም አሳንስር አምራች ኩባንያ ሲሆን ስሙም ዳን ሊፍት ይባላል።
ይህ ሀገር በቀል ድርጅት በቴክኖሎጂ አለመዘመን ምክንያት ከውጭ የሊፍት ኩባንያዎች ጋር ለመወዳደር ሲቸገር የቆየ ሲሆን ፍላጎቱንም ለመሸፈን ሳይችል ቆይቷል።
የእስያ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያለውን የአሳንስር ፍላጎት የሚሸፍኑ ሲሆን በተለይም የቻይና እና ደቡብ ኮሪያ ኩባንያዎች ሰፊ የገበያ ሽፋን አላቸው።