በኢትዮጵያ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጠውን የበይነ-መረብ ትምህርት ለማጠናከር የሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ /AI) ቴክኖሎጂን ለመጠቀም የሚያስችል ሀገር አቀፍ እና ተቋማዊ ፖሊሲ በመዘጋጀት ላይ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር ገልጿል።
በሚኒስቴሩ የበይነ-መረብ ትምህርት ማጠናከር ፕሮግራም የክትትል፣ ግምገማ እና ትምህርት ዋና አማካሪ ዶክተር ጌታሁን መኮንን እንደተናገሩት፤ ቴክኖሎጂው በዘመናዊው የመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ አለው።
ሆኖም አጠቃቀሙ በግልጽ መመሪያ እና ደረጃ ካልተመራ ክፍተቶችን ሊፈጥር እንደሚችል ጠቁመዋል።
በተለይም በተማሪዎች ምዘና ወቅት የሚቀርቡ ሥራዎች በተማሪዎቹ ጥረት የተከናወኑ መሆናቸውን ለማረጋገጥና አሉታዊ ተጽዕኖውን ለመከላከል ጥብቅ ቁጥጥር ያስፈልጋል ተብሏል።
አሰራሩ ከተቋም እስከ ግለሰብ የሥነ-ምግባር ደንቦችን ተከተሎ ሥራ ላይ መዋል እንዳለበትና ቴክኖሎጂውን ጨርሶ አለመጠቀም ወይም ልቅ ማድረግ ተገቢ አለመሆኑን አማካሪው ገልጸዋል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት ተማሪዎች እንደ ፍላጎታቸው እና የዕውቀት ደረጃቸው የተዘጋጀ የመማሪያ ስልት እንዲኖራቸው የማስቻል አቅም እንዳለውም ተገልጿል።
ዶክተር ጌታሁን አክለውም፤ ቴክኖሎጂው ተማሪዎች ደካማ የሆኑባቸውን የትምህርት ዘርፎች በመለየት ተጨማሪ የመማሪያ ጭብጦችንና መጻሕፍትን ለመጠቆም የበይነ መረብ ወይም ኦንላየን ትምህርት ሥርዓቱን ያፋጥናል ብለዋል።
ዓለም የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ደረጃ በአግባቡ አለመጠቀም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያስተጓጉለውም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ለኤአይ ልዩ ትኩረት የሰጠች ሲሆን ከሁለት ዓመት በፊት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን አቋቁማለች።
ከዚህ በተጨማሪም በአፍሪካ የመጀመሪያው የኤአይ ዩንቨርስቲ በማቋቋም ላይ ስትሆን የቦታ መረጣ ተጠናቆ የዩንቨርሲቲው ግንባታ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ይህ ዩንቨርስቲ የቴክኖሎጂ ተሰጥኦ ያላቸው ኢትዮጵያዊያንን ከማሰልጠን በተጨማሪ ለአፍሪካዊያን የስኮላርሽፕ እድል የመስጠት እቅድ እንዳለው ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ባሳለፍነው ሰኔ ወር ላይ በፓርላማ ተገኝተው የመንግስታቸው ዓመታዊ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት መናገራቸው ይታወሳል።