የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙን ተከትሎ በተወሰዱ ጥብቅ የፖሊሲ እርምጃዎች የዋጋ ንረቱን ወደ ነጠላ አሀዝ ማውረድ ተችሎ እንደነበር ያሱት የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ፣ አሁን ግን ተመልሶ ማሻቀቡን ገልጸዋል።
ዶክተር ኢዮብ ይህን የተናገሩት ዛሬ መስከረም 19 ቀን 2019 ዓ.ም በተጀመረው ሁለተኛው የፋይናንስ ፎረም መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ነው።
ዶክተር እዮብ ማሞ አክለውም ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር ላይ የዋጋ ንረቱ ወደ 9 ነጥብ 7 በመቶ ዝቅ ብሎ የነበረ ቢሆንም፣ ባሳለፍነው ነሀሴ ላይ ግን ተመልሶ 15 ነጥብ 1 በመቶ መድረሱን አስረድተዋል።
ቀደም ሲል የታየው በጎ ውጤት ሪፎርሙን ተከትሎ በተወሰዱ ተከታታይ የፖሊሲ እርምጃዎች የተገኘ መሆኑን ያብራሩት ገዢው፤ አሁን ያጋጠመው ጭማሪ በፖሊሲ ውድቀት ሳይሆን በውጫዊ ችግሮች ምክንያት የመጣ በመሆኑ፣ ሁኔታውን በተከታታይ ጥብቅ የቁጥጥር ስራዎች ለማስተካከል እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ባሳለፍነው ሰኔ ወር ላይ የወለድና የብድር ምጣኔ ለውጥን ጨምሮ በገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው የተወሰዱ ተከታታይ እርምጃዎች የዚሁ የቁጥጥር አካል መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ አድዋ ሙዚየም አዳራሽ እየተካሄደ ባለው በዚህ ጉባኤ ላይ የባንክ ፕሬዝዳንቶች ፣ የፋይናንስ ባለሙያዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች እና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።