በሽታው ላለፉት ተከታታይ ሶስት አመታት ከጨመረ በኋላ በከፍተኛ መጠን ቀንሶ እንደነበር ከሰሞኑ በሆሳዕና በተካሄደ የ2018 ዓመታዊ የጤና ዘርፍ የግምገማ መድረክ የገለጹት ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበጀት ዓመቱ 6 ነጥብ 8 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች በወባ መያዛቸውን ተናግረዋል።
ቁጥሩ በ2017 ከነበረው በ37 በመቶ ቀንሷል ያሉት ሚኒስትሯ በባለፉት 3 አመታት ከነበረው በእጥፍ እጥፍ መቀነስ መቻሉንና በወባ ምክንያት የሚሞቱ ወገኖች ቁጥርም ከነበረበት ከ50% በላይ ስለመቀነሱ ገልጸዋል።
ሆኖም “በአመቱ ከ6 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎቻችን ዛሬም በወባ በመያዛቸው ትንሽ ቁጥር የማንለው መሆኑ ሊታወቅ ይገባል” ያሉት ሚኒስትሯ በወባ ምክንያት የሚያጋጥመው ሞት ከድሮው አንጻር አነስተኛ ቢሆንም በዓመቱ ውስጥ 378 ሞቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
ዶ/ር መቅደስ ዛሬም በ134 ወረዳዎች የወባና ውሃ ወለድ ወረርሽኞች አሉ ያሉም ሲሆን ከዚሁ ጋር በተያያዘ የ258 ሰዎች ህይወት ማለፉን ጠቁመዋል።
የወባ ስርጭትን ለመግታት በየደረጃው ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ቢሆንም ማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄዎችን በመፍጠርና የመከላከያ ስራዎችን በማስፋት መከላከልና አክሞ ማዳኑ ላይ አተኩረን ልንሰራ እንደሚገባ መንግስት ያምናል ያሉም ሲሆን ከ14 ሚሊየን በላይ ተጨማሪ አጎበሮች መሰራጨታቸውን ገልጸዋል።
70 በመቶና ከዚያ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ የአየር ንብረት የወባ ተጋላጭነቱን ከፍ እንዳደረገው በመግለጽም ከማህበረሰቡ ጋር በጋራ ለመስራት ጥሪ አቅርበዋል።
በአዲስ መልክ ወደ ተግባር በሚገባው በሁለተኛው የጤና ዘርፍ የኢንቨስትመንት ዕቅድ ፍትሐዊ፣ ጥራቱ የተጠበቀ፣ የማይበገርና ምላሽ ሰጪ የጤና ሥርዓትን ለመገንባት ስለመታሰቡ በመጠቆምም የወባ ወረርሽኝን ከመከላከል ባለፈ የተጋላጮቹን ቁጥር በ1000 ሰዎች ወደ 66 ለማውረድ ግብ አስቀምጠናል ብለዋል።