በኦሮሚያ ክልል ሲርካ ወረዳ 48 ሰዎች መገደላቸውን ኢሰመኮ ገለጸ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል የቀድሞ አርሲ ዞን በአዲሱ አደረጃጀት ደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን ሲርካ ወረዳ ቢርቦና ጮሌ ቀበሌ ጥቅምት 14 ቀን 2019 ዓ.ም. የተፈጸመው ጥቃት ያስከተለውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በተመለከተ ያደረገውን ምርመራ ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡

በዚህም መሠረት በዕለቱ በደረሱ ጥቃቶች በሰዎች ላይ ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ መፈናቀል እና የንብረት ውድመት የደረሰ መሆኑን ኢሰመኮ በአካባቢው በአካል በመገኘት ከተጎጂዎች፣ ከተጎጂ ቤተሰቦች፣ ከዐይን እማኞች፥ ከማኀበረሰብ ተወካዮች፥ ከሃይማኖት ተቋማት ኃላፊዎች፤ በሕክምና ተቋማት ሕክምና ከሚከታተሉ ተጎጂዎች እና ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት መረጃዎችን ማሰባሰቡን ገልጿል።

እንዲሁም የመስክ ምልከታ በማድረግና የዲጂታል የምርመራ ስልት ተግባራዊ በማድረግ ግድያዎቹ መፈጸማቸውን እንዳረጋገጠ ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ኢሰመኮ አከናወንኩት ባለው ምርመራ በክልሉ ደቡብ ምሥራቅ ዞን ሲርካ ወረዳ፣ ቢርቦና ጮሌ ቀበሌ ጥቅምት 14 ቀን 2019 ዓ.ም. ከጠዋቱ 12፡30 ሰዓት እስከ ጠዋቱ 2፡30 ሰዓት ድረስ በአከባቢው ታጥቆ የሚቀሳቀሰው እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራ (በተለምዶ ‘’ኦነግ ሸኔ’’) ታጣቂ ቡድን ወደ ቀበሌው በአራት አቅጣጫ በመግባት በፈጸመው ጥቃት 23 በቀበሌ ደረጃ የተደራጁ ጸጥታ አካላት፥ 5 የሚሊሻ አባላት እንዲሁም 13 ሰላማዊ ሰዎች ሕይወት ማለፉን በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል። ከተጠቀሱት 13 ሕይወታቸው ካለፉት ሲቪል ሰዎች በተጨማሪም በአካባቢው በታጠቁ ኢመደበኛ በሆኑ ታጣቂ ግለሰቦች 7 ሲቪል ሰዎች መገደላቸውንም ኮሚሽኑ ጠቅሷል።

በተጨማሪም በኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን በተፈጸመ ጥቃት በ20 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ሲደርስ 21 መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል፤ 247 ቤተሰቦች ከአካባቢው ሲፈናቀሉ ለጊዜው ቁጥራቸው ያልተለዩ የቀንድና የጋማ ከብቶችም መዘረፋቸው ተገልጻል።

ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምሥራቅ ዞን፣ ሲርካ ወረዳ፣ ቢርቦና ጮሌ ቀበሌ ባደረገው ምርመራ በአካባቢው ግለሰቦች ኢመደበኛ በሆነ መንገድ ታጥቀው በስፋት የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን በምርመራ ሪፖርቱ ማረጋገጡንም ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ኢሰመኮ በኦሮሚያ ክልል፣ የቀድሞ አርሲ ዞን፣ በአሰኮ፣ በአንቆሎ ዋቤ፣ በጉና እና በመርቲ ወረዳዎች በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ጥቃቶችን በተመለከተ፣ መንግሥት ጥቃቶቹን ለመከላከል፣ የሰዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ እና ጥቃት ፈጻሚዎችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ በተደጋጋሚ ማሳሰቡ ይታወሳል።

መንግሥት የሕይወት፣ የንብረት፥ የአካል ደኅንነትና የነጻነት መብቶችን የማክበር፣ የመጠበቅና የማሟላት ኃላፊነት በሕገ መንግሥቱ መሠረት በሁሉም የፌዴራልና የክልል የመንግሥት አካላት ላይ የተጣለ ግዴታ ሲሆን ጥሰቶችን ከማጣራትና ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ ጥቃቶች ዳግም እንዳይከሰቱ የሚያስችሉ ዘላቂ የመከላከል እርምጃዎችን መውሰድም ይጠበቅበታል ተብሏል።

እንዲሁም ከመንግሥት የጸጥታ አደረጃጀት ውጭ ያሉ ኢመደበኛ የታጠቁ አካላትን በተመለከተ አስፈላጊውን ክትትል ሊያደርግ ይገባል ሲልም ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በነዋሪዎች ላይ የደረሱት ግድያዎች፣ የአካል ጉዳቶች፣ የንብረት ውድመትና መፈናቀል እጅግ አሳሳቢ መሆናቸውን ገልጸው መንግሥት በጥቃቱ የተጎዱና ተመሳሳይ የጸጥታ ስጋት ባለባቸው አከባቢዎች ሁሉ በቂና ውጤታማ የሆነ ጥበቃ ሊያደርግ፤ በተለይም የአካባቢው የጸጥታ አካላት አደረጃጃቶችን በመገምገም እና በማስተካከል የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶችን በማጠናከር ለሚከሰቱ ስጋቶች ፈጣን ምላሽ በመስጠት የነዋሪዎች የሕይወት፣ የአካል ደኅንነትና፣ ንብረት የመጠበቅ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽነሩ አክለዉም በጥቃቱ ለደረሰዉ ጉዳት ፈጣን ገለልተኛና ውጤታማ ምርመራ በማካሄድ ተጠያቂነትን ሊያረጋግጥ፣ ለሟቾች ቤተሰቦች እና ለተገጂዎች አስፈላጊ ድጋፎችን እንዲያደርግ፤ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ የሚያስችል እንዲሁም ተጎጂዎችን ለመካስና ለማቋቋም የሚያስችሉ አፋጣኝ እርምጃዎች ሊወስድ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ኢሰመኮ በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምሥራቅ ዞን በተለያዩ ወረዳዎችና ጊዜያት የተፈጸሙ ጥቃቶች ያስከተሏቸውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችና መንስዔዎች በተመለከተ ሲያከናዉን የቆየውን ሥልታዊ ምርመራ እያጠናቀቀ ሲሆን የምርመራ ሪፖርቱ ዝግጅት እንደተጠናቀቀ ሪፖርቱን ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

እንዲሁም ኮሚሽኑ በጋምቤላ፣ በኦሮሚያና ሶማሊ ክልሎች አዋሳች ወረዳዎች፣ በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ላይ የደረሰውን ጥቃት እንዲሁም በትግራይ ክልል ከተካሄደው ግጭት ጋር ተያይዞ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን አስመልክቶ ምርመራና ክትትል እያደረገ መሆኑንም ገልጿል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *