ፖሊስ ከ40 ሺህ በላይ ዜጎችን በህገወጥ መንገድ ያዘዋወሩ ተጠርጣሪዎች መያዙን ገለጸ

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ” ከ60 በላይ ስደተኞች ለሞት እና በርካታ ሴቶች ለመደፈር ተጠያቂ ናቸው ” ያላቸውን 17 አደገኛ ተጠርጣሪ የሰዎች አዘዋዋሪዎች መያዙን አስታውቋል።

ፖሊስ እንደገለጸው፣ በ”መሐመድ ጣሂር አደም (ወርዲ)” የሚመራው ቡድን ሰዎችን ከኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በደላሎች አማካኝነት በመልመል በጂቡቲና በየመን በኩል በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ያዘዋውር ነበር።

እነዚህ አዘዋዋሪዎች ከ40 ሺህ በላይ ሰዎችን በህገወጥ መንገድ እንዳዘዋወሩ እና ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ በሕገ-ወጥ መንገድ እንደሰበሰቡ ተገልጿል።

ተጎጂዎች በየመን ውስጥ በመጋዘኖች ታግተው ድብደባ፣ ማሰቃየት እና ሌሎች ኢሰብአዊ ድርጊቶች እንደተፈጸሙባቸው ሲገለጽ፣ ቤተሰቦቻቸውን ገንዘብ እንዲልኩ ለማስገደድ የስቃይ ቪዲዮዎች ይላኩ እንደነበር ተጠቁሟል።

በምርመራውም ከ60 በላይ ሰዎች መሞታቸውና በርካታ ሴቶች መደፈራቸው መረጋገጡን ፖሊስ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

የፌደራል ፖሊስ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ጄይላን አብዲ፣ ተጠርጣሪዎቹ ሰሞኑን ለ15 ቀናት በቆየ ኦፕሬሽን በአዲስ አበባ፣ በሐረሪና በሌሎች አካባቢዎች መያዛቸውን ገልጸዋል።

ፖሊስ የተጠርጣሪዎቹ የምርመራ ፋይል ለፍትሕ ሚኒስቴር መተላለፉን አስታውቋል።

በስማቸው የነበሩ ቤቶች ፣ ተሽከርካሪዎች እና ሌሎች ንብረቶችም እንዳይዘዋወሩ መታገዳቸውን ፖሊስ ገልጿል።

ፌደራል ፖሊስ ከህገወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር በተያያዘ በርካታ እርምጃዎችን እየሰወደ ሲሆን ከአንድ ሳምንት በፊት በተባበሩት አረብ ኢምሬት ዱባይ ኢትዮጵያዊያንን በህገወጥ መንገድ እንዲመጡ በማድረግ ለጉልበት ብዝበዛ እና የገንዘብ ማጭበርበር ይፈለጉ የነበሩ ተጠርጣሪዎችን ወደ አዲስ አበባ ማምጣቱ ይታወሳል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *