ኢትዮጵያ በሱዳን የተነሳትን ክስ ውድቅ አደረገች

ከሰሞኑ በጀነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር ከባህርዳር የተነሱ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ካርቱም ኤርፖርት ላይ ጥቃት አድርሰዋል የሚል ክስ አቅርቦ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና መከላከያ ሚኒስቴር በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ እና የሱዳን ህዝቦች ያላቸውን ታሪካዊ ግንኙነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት አንዳንድ ታጣቂዎች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት በመጣስ የሚያደርጉትን ትንኮሳ ለህዝብ ይፋ ከማድረግ መቆጠቡን አንስቷል፡፡

የሱዳን ጦር የህወሃት ቅጥረኛ ወታደሮችን በእርስ በርስ ጦርነቱ ውስጥ ማሳተፉን እና ለእነዚህ ቅጥረኛ ወታደሮች  የጦር መሳሪያ እና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ በምዕራብ ኢትዮጵያ ትንኮሳ እንዲፈፅሙ ማድረጉን በመግለጫው ላይ ጠቅሷል፡፡

በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት የህወሃት ቅጥረኛ ወታደሮች በግልፅ ሲንቀሳቀሱ መታየታቸው ሱዳን ለተለያዩ ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች መናኸሪያ ሆና እያገለገለች መሆኗን የሚያሳይ ታማኝ መረጃ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

መሰል ድርጊቶች እና ቀደም ሲል በሱዳን ጦር እና ባለስልጣናት የተሰነዘሩ ውንጀላዎች እኩይ አጀንዳዎችን ለማራመድ የሚፈልጉ የውጭ ኃይሎችን ዓላማ ለማሳካት ያለመ መሆኑ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከሱዳን ህዝቦች ጋር አጋርነቷን እና ያላትን ወዳጅነት አጠናክራ ትቀጥላለች ያለው መግለጫው ኢትዮጵያ የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት በውይይት ይፈታል ብላ እንደምታምንም አስገንዝቧል፡፡

በተጨማሪ ኢትዮጵያ በሱዳን የሲቪል መንግሥት እንዲመሰረት፣ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ እና ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ እንዲሁም ነጻ፣ ሁሉን አቀፍ እና ግልጽ ሲቪል መር ውይይት ማድረግ አስፈላጊ ነው ብላ እንደምታምን ሁለቱ ተቋማት በጋራ ያወጡት መግለጫ ያስረዳል፡፡

ከሶት ዓመት በፊት የተጀመረው የሱዳን የእርስ በዕርስ ጦርነት የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት እንዳለበት ሲገለጽ የቆየ ሲሆን የጦርነቱ ተጽዕኖ ኢትዮጵያ፣ ቻድ፣ ግብጽ እና ሌሎችም ሀገራት ላይ ጉዳቶችን አስከትሏል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *