“ጁንቱ ቴክኖሎጂስ ግሩፕ” የ“ቼሪ” አውቶሞቢል ኩባንያ (Chery Automobile) ምርቶችን ለኢትዮጵያ ገበያ ማቅረብ መጀመሩን አስታወቀ፡፡
ድርጅቱ “ኦሞዳ” (OMODA E5) እና “ጃይኮ” (JAECOO J5) የተሰኙትንና የ“ቼሪ” ምርቶች የሆኑትን ሁለት የኤሌክትሪክ መኪና ሞዴሎችን ለኢትዮጵያ ገበያ በማቅረብ የዘመናዊ ተሽከርካሪዎች ወኪል አቅራቢነቱን ማስፋፋቱን ገልጿል፡፡
ድርጅቱ ስራውን በዓለም አቀፍ ደረጃ በታወቀ አገልግሎት፣ በላቀ ቴክኖሎጂ እና በረጅም ጊዜ የገበያ ኢንቨስትመንት ለመምራትም “የጁንቱ-ኦሞዳ-ጃይኮ” የምርት ማሳያ (ሾውሩም) እና የድህረ ሽያጭ አገልግሎት ማዕከሉን ሰሞኑን ስራ አስጀምሯል።
የጁንቱ ቴክኖሎጂስ ትሬዲንግ የኦሞዳ እና ጃይኮ ቅርንጫፍ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ክንዴ መቻል፣ ጁንቱ ቴክኖሎጂስ ከሁለት ወራት በፊት አራት ዓይነት የ“ጂ.ኤ.ሲ” (GAC) የኤሌክትሪክ መኪና ሞዴሎችን ለገበያ ማቅረቡን አስታውሰው፣ በቅርቡ ደግሞ “ኦሞዳ” እና “ጃይኮ” የተሰኙትና የ“ቼሪ አውቶሞቢል” ኩባንያ ምርቶች የሆኑት የኤሌክትሪክ መኪና ሞዴሎች የኢትዮጵያን ገበያ እንዲቀላቀሉ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡
የጁንቱ-ኦሞዳ-ጃይኮ የምርት ማሳያ (ሾውሩም) እና የድህረ ሽያጭ አገልግሎት ማዕከሉ ጥገናና መለዋወጫን ጨምሮ ዘመናዊ መሰረተ ልማቶችና አገልግሎቶች የተሟሉለት እና ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የተሞክሮ ማዕከል የሚሆን ስፍራ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
ይህ ኢንቨስትመንት የስራ እድሎችን ከመፍጠርና የክህሎት ልማትን ከመደገፍ ባሻገር፣ ለኢትዮጵያ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ዘመናዊነት የጎላ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክትም አመልክተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አዲስ አበባ ከተማ ለዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት እንዲሁም ለዘመናዊና የታዳሽ ኃይል የትራንስፖርት አማራጮች ያላትን አመቺነት ይበልጥ እንደሚያጎለብተውም ገልፀዋል፡፡
“ጁንቱ ቴክኖሎጂ ትሬዲንግ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያተረፉ የመኪና ብራንዶችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ለኢትዮጵያውያን ደንበኞች ሰፊና አስተማማኝ የትራንስፖርት አማራጮችን ለማቅረብ ያለውን ቁርጠኛነት አረጋግጧል” ብለዋል፡፡
መንግሥት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ማበረታታቱ ለሀገሪቱ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ገልፀው፣ ድርጅቱ በቀጣይም ለኢትዮጵያ ገበያ የሚያቀርባቸው መኪኖች የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ግብ የሚያግዙ እና የሀገሪቱን መስፈርት የሚያሟሉ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡
ጁንቱ ዓለም አቀፍ የፈጠራ ውጤቶችን ከአካባቢያዊ የገበያ ግንዛቤ ጋር በማቀናጀት የነዳጅ ጥገኝነትን ለመቀነስ እና የትራንስፖርት ሥርዓቶችን ለማዘመን የሚደረጉ ሀገራዊ ጥረቶችን በመደገፍ፣ ኢትዮጵያ ወደ ታዳሽ ኃይል ትራንስፖርት ለምታደርገው ሽግግር ሁነኛ አጋር ሆኖ እንደሚቀጥል አቶ ክንዴ ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም ኢትዮጵያ ውስጥ የመኪና ማምረቻና መገጣጠሚያ ፋብሪካ በመገንባት በኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ትልቅ አሻራ ለማሳረፍ ማቀዱንም አመልክተዋል፡፡
እንደሳቸው ገለጻ፣ በኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ትራንስፖርት ዘርፍ ለሚሰማሩ ኩባንያዎች ምቹ የኢንቨስትመንት እድሎች አሉ፡፡ መንግሥት የወሰዳቸው ተግባራዊ እርምጃዎች የዘርፉን የኢንቨስትመንት አቅምና እድል አሳድገውታል፡፡ ጁንቱም እነዚህን የኢንቨስትመንት እድሎች በመጠቀም ለኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የበኩሉን አስተዋፅዖ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ለታዳሽ ኃይል ላይ ለተመሰረተና ለአካባቢ ተስማሚ ለሆነ የትራንስፖርት ዘርፍ እድገት ያሳየው ቁርጠኛነት እንዲሁም በሀገሪቱ ታዳሽ የኃይል አማራጮችን ለሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች ያለው ፍላጎት ማደጉ ኩባንያው ስራውን በኢትዮጵያ እንዲያስፋፋ እንዳበረታታው አስረድተዋል፡፡ መንግሥት ለድርጀቱ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝም አቶ ክንዴ ገልጸዋል፡፡

የቼሪ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሉካስ ያዎ በበኩላቸው፣ ቼሪ “ኦሞዳ” (OMODA E5) እና “ጃይኮ” (JAECOO J5) ሞዴሎችን ለኢትዮጵያ ገበያ ማቅረቡ ኩባንያው ዓለም አቀፍ ደንበኞቹ ዘመናዊና የተሻለ የፕሪሚየም አውሞቲቭ ልምድ እንዲኖራቸው የያዘው ስትራቴጂካዊ ርምጃው እቅድ አካል ነው ብለዋል፡፡
የምርት ማሳያ (ሾውሩም) እና የድህረ ሽያጭ አገልግሎት ማዕከሉ መከፈት ቼሪ አውቶሞቢል ኩባንያ ገበያውንና የገዢዎችን አማራጭ ለማስፋት ያለውን ቁርጠኛነት እንደሚያሳይ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ትልቅ የገበያ አቅም እንዳላት አመልክተው፤ ኢኮኖሚዋ በፍጥነት እያደገ፣ የነዋሪዎች የኑሮ ደረጃ እየተሻሻለ እና የኤሌክትሪክ መኪና ፍላጎትም በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱንም ጠቁመዋል፡፡
ሁለቱም ብራንዶች እጅግ ዘመናዊ፣ ምቹና አስተማማኝ ምርቶች መሆናቸውን ገልጸው፣ “በአስተማማኝ የምርት ጥራት እና የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም ከጁንቱ ቴክኖሎጂ ጋር በሚደረግ ትብብር የደንበኞችን እምነት በቀላሉ እናገኛለን፤ የኢትዮጵያውያንንም ኑሮ ምቹና ዘመናዊ እናደርጋለን” ብለዋል፡፡
ቼሪ አውቶሞቢል ግሩፕ እ.አ.አ በ1997 ውሁ፣ ቻይና ውስጥ የተቋቋመ ሲሆን፣ ኩባንያው በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም ከሚታወቁ መኪና አምራች ድርጅቶች መካከል አንዱ መሆን ችሏል፡፡ ኩባንያው ብርቱ የገበያ ፉክክር ባለበት ጠንካራ ተፎካካሪ መሆኑን በተግባር አስመስክሯል፡፡
እ.አ.አ በ2025 ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ሽያጭ ማከናወኑንና ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ለውጭ ገበያ የቀረበ ነው፡፡ በ2026 የ3 ሚሊዮን ሽያጭ ለማከናወንና 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን መኪኖችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ አቅዷል፡፡ በዚህም ላለፉት ተከታታይ 24 ዓመታት ግንባር ቀደሙ የቻይና የጉዞ መኪኖች ላኪ ኩባንያ ሆኖ ለመቀጠል የሚያስችለውን ስኬት ያስመዘግባል፡፡