ዓለም ባንክ ከአንድ ወር በኋላ ለኢትዮጵያ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር በጀት ድጋፍ ሊያጸድቅ መሆኑን ገልጿል።
አንድ የባንኩ ከፍተኛ ባለሙያ ሲናገሩ አዲስ ማለዳ ሰምታለች።
የገንዘብ ሚኒስቴር ከሳምንት በፊት የ2019 ዓ.ም የበጀት ረቂቀን ለምክር ቤቱ ባቀረበበት ወቅት ከ2.3 ትሪሊዮን ብር በላይ መሆኑን ገልፆ የበጀት ጉድለቱ ከውጭ እርዳታ እና ሀገር ውስጥ በሚገኝባቸው ገቢ ይሸፈናል ማለቱ ይታወሳል።
በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ቢሮ የግሉ ዘርፍ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ብስራት ተሾመ እንደገለጹት ከሆነ ባንኩ ለኢትዮጵያ መንግስት የሚውል የአንድ ጊዜ የበጀት ድጋፍ በማዘጋጀት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለሙያው ይህን ያሉት ትናንት ሰኔ 10 ቀን 2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ ነው።
የዓለም ባንክ ባለሙያዎች እያዘጋጁት ያለው የበጀት ድጋፍ በቀጣይ እ.አ.አ ሰኔ 25 በሚደረገው የዓለም ባንክ ቦርድ ስብሰባ ላይ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል ተብሏል።
ለኢትዮጵያ ይሰጣል የተባለው የ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር አሁን ባለው የምንዛሬ ተመን ከ229 ቢሊዮን ብር በላይ ይሆናል።
ዓለም ባንክ እስካሁን ድረስ ለኢትዮጵያ “ዕድገትና የወደፊት ጉዞ ያለውን ቁርጠኝነት” ለማሳየት፣ ወደ 17 ቢሊዮን ዶላር የሚሆን የብድርና የእርዳታ ድጋፎችን እያቀረበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ሆኖም እነዚህ ድጋፎች ቀጣይነት ሊኖራቸው የሚችለው በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ሲሰፍንና መንግስት የጀመራቸውን በርካታ የሪፎርም ሥራዎች አጠናክሮ ሲቀጥል ብቻ እንደሆነ ተመላክቷል።
በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በርካታ የፖሊሲ የመመሪያ እና ደንብ ለውጦች በአንድ ጊዜ እየተካሄዱ ይገኛል ያሉ ሲሆን ከዚህም ውስጥ የውጭ ምንዛሬ ሪፎርም አንዱ መሆኑ ተገልጻል። ሁለት ዓመት ሊሞላው ወራት የቀሩት የኢትዮጵያ ሪፎርም ማሻሻያው፣ በተለይም በማኑፋክቸሪንግና በንግድ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ የግሉ ክፍለ አካላት ጠቃሚ ውጤት እያስገኘ የሚገኝ ሪፎርም ነው ብለውታል።
የዓለም ባንኩ ባልደረባ አክለውም የጉምሩክ አሰራር ለውጥ ተደርጓል ያሉ ሲሆን ቀደም ሲል የጉምሩክ ባለሙያዎች በራሳቸው መረጃ ከጎግል ዋጋ የሚያወጡ ወይም ጎግል በማድረግ ይተገብሩት የነበረውን አሰራር በማስቀረት፣ አስመጪው ወይም አምራቹ የሚያመጣውን ትክክለኛ የኢንቮይስ ዋጋ ተጠቅመው እንዲሰሩ የሚያስገድድ ማሻሻያ ተደርጓልም ብሏል።
ሌላው ደግሞ ኢትዮጵያ የፋይናንስና የሎጂስቲክስ ፖሊሲዎችን በማሻሻል ለዓለም አቀፍ ተወዳዳሪዎች ክፍት መደረጉ እንደሆነ አቶ ብስራት ገልጸዋል። አክለውም የባንክ፣ የፋይናንስ፣ የኢንሹራንስ እንዲሁም በቅርቡ ደግሞ የሎጂስቲክስ ዘርፍ ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እና ለጭነት አስተላላፊዎች ክፍት መደረጉ ለትብብሩ አንዱ መነሻ መሆኑ ተገልጿል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ በሎጂስቲክስ ዘርፍ ላይ ለመሰማራት የሚያስፈልጉት አነስተኛ መስፈርቶች በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀነሱ ተደርጓል ያሉ ሲሆን እነዚህ ሪፎርሞች መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የጀመረቻቸው ሰፊ ሪፎርሞች በሰላምና መረጋጋት እጦት ምክንያት ወደ ኋላ እንዲመለሱ ባንኩ እንደማይፈልግ እና የንግዱ ማህበረሰብ የተሻለ፣ ተገማች እና በውድድር የሚመራ የንግድ ስርዓት እንዲኖር የዓለም ባንክ ድጋፉውን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።