ለአዲሰ አበባ ከተማ ዓመታዊ በጀት 502 ቢሊዮን ብር ተመደበ

ከተመደበው በጀት ውስጥ ትልቁን ድርሻ የያዘው ለድህነት ቅነሳና ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ በሚል የተመደበው ነው ተብሏል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ዛሬ ሰኔ 12፣ 2018 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው፤ የከተማዋን የ2019 ዓ.ም ረቂቅ በጀትን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

በዚህም መሰረት ሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚጀምረው የ2019 በጀት ዓመት የአዲስ አበባ ከተማ በጀት 502 ነጥብ 27 ቢሊዮን ብር ሆኖ ወደ ምክር ቤት እንዲመራ መመርያ ሰጥቷል ።

ረቂቅ በጀቱ የከተማ አስተዳደሩን የልማት ስትራቴጂዎች እና የትኩረት አቅጣጫዎች፣ድህነትን ለመቀነስ፣ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማረጋገጥ ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነ ተዘርዝሯል።

በተጨማሪም የከተማውን ነዋሪ የልማት ፍላጎትና የአገልግሎት አቅርቦት ለማሳደግ በተለይም  የስራ እድል ፈጠራን ለሚያበረታቱ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ማለትም መንገድ፣ ውሃ፣ መኖሪያ ቤት፣ ፅዳት፣ ትራንስፖርትና የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከልን ታሳቢ ማድረጉ ተገልጿል።

ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማሻሻል ሚና ላላቸዉ ዘርፎች ትምህርት፣ ጤና እና በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ የከተማዋ ነዋሪዎች የሚደረግ ድጎማን ማካተቱን የከንቲባ ጸህፈት ቤት ተናግሯል።

በዚሁ መሰረት ገንዘቡ በከተማው አስተዳደር ለማዕከል ሴክተር ተቋማትና ለክፍለ ከተሞች ለመደበኛና ለካፒታል ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያነት ይውላል ይላል።

ከተደለደለው አጠቃላይ ወጪ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ወይንም 71 በመቶ ለድህነት ቅነሳና ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ የተመደበ ሲሆን ቀሪው 29 በመቶ ደግሞ ለአስተዳደራዊ ወጪዎች መደልደሉ ተነግሯል።

የፌደራል መንግሥት ለ2019 በጀት ዓመት 2 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ብር የያዘ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 2 ትሪሊዮን ገደማው ከታክስ ለመሰብሰብ ታቅዷል። ግማሽ ትሪሊዮን ያህሉ ገንዘብ ደግሞ ለእዳ ክፍያ እንደሚውልም ተገልጿል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *