ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ ወራት ውስጥ ከኪሳራ ወደ ትርፍ እንደሚሸጋገር አስታወቀ

ከአምስት ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ የገባው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት ከሶስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማድረጉን ገልጿል።

ለኢንቨስትመንት ያወጣውን ወጪ ሳይመልስ የቆየው ኩባንያው ኪሳራው እየቀነሰ መምጣቱን ገልጾ በቀጣዮቹ ወራት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ትርፍ እንደሚገባ አስታውቋል።

መጋቢት 30 በተጠናቀቀው የኩባንያው በጀት ዓመት 15.9 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱን ይህም ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲመሳከር የ130 በመቶ ብለጫ አንዳለው የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ዊም ቫንሄሌፑት ገልጸዋል፡፡

በጊዜው ኩባንያው 39.5 ቢሊዮን የኬንያ ሽልንግ ወይም 47.7 ቢሊዮን ብር አካከባቢ ኪሳራ አስመዝግቧል፡፡

ኪሳራው አምና በተመሳሳይ ጊዜ ከተመዘገበው በግማሽ ያህል መቀነሱንም ዋና ስራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል፡፡

ኩባንያው በዓመቱ ውስጥ ካገኘው 15.9 ቢሊዮን ብር ውስጥ 9.6 ቢሊዮን  ብር ወይም ከ67 በመቶ በላይ ገቢው የተገኘው ከሞባይል ዳታ ሲሆን፣ 3 ቢሊዮን ብር ወይም 20 በመቶው ደግሞ ከድምጽ የተገኘ ነው ተብሏል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም 1400 ማማዎች ላይ ኔትወርክ መዘርጋቱን የተናገረው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ለዚህም በየዓመቱ እስከ 6 ቢሊዮን ብር ለኪራይ አንየከፈልኩ ነው ብሏል።

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የ3 ወራት ንቁ ደንበኞች ቁጥር 13.6 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ54.2 በመቶ እድገት አሳይቷል።

የኤምፔሳ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከእጥፍ በላይ በመጨመር 5.2 ሚሊዮን ደርሷል፣ በኤምፔሳ መተግበሪያ የተደረገው የገንዘብ ዝውውርም 32.5 ቢሊየን ብር ደርሷል ተብሏል፡፡

ኩባንያው ከመላው የሀገሪቱ ህዝብ 59.2 በመቶ የሚሆነውን የ4G ኔትወርክ ተጠቃሚ ማድረግ ችያለሁ ብሏል።

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ሀምሌ 2013 በኢትዮጵያ የግል ቴሌኮም አገልግሎት ታሪክ የመጀመሪያ ተቋም በመሆን በኢትዮጵያ ፈቃድ ያገኘ ሲሆን ነሀሴ 2014 በድሬዳዋ ከተማ የመጀመሪያውን የቴሌኮም አገልግሎት በመስጠት ስራ ጀምሯል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *