የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአማራ እና ትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሱባቸው አካባቢዎች ምርጫ እንዲካሄው ውስኗል ተብሏል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ የካቲት 16፣ 2018 ባወጣው መግለጫ ከዚህ በፊት በትግራይ ክልል ስር ሆነው ምርጫ ሲካሄድባቸው የነበሩ ምርጫ ክልሎች ከክልሉ መንግስት ውጪ ሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ እንዲካሄድባቸው መወሰኑን የሚገልጽ ደብዳቤ እንደደረሰው ገልጿል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብቻ ይካሄድባቸዋል ተብለው በቦርዱ መግለጫ ላይ የተጠቀሱት ምርጫ ክልሎች ሁመራ፣ አዲረመጽ፣ ኮረምኦፍላ ፣ ጠለምት እና ራያ አላማጣ ምርጫ ክልሎች እንደሆኑም ቦርዱ አስታውቋል፡፡
ቦርዱ አክሎም የክልል ምክር ቤት ምርጫ በአካባቢዎቹ ላይ የተነሳባው የይገባኛል ውዝግብ ጥያቄ በህገ መንግስት ውሳኔ መሰረት ሲፈታ እንደሚካሄድ ቦርዱ አስታውቋል።የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳድር በበኩሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን ተቃውሟል፡፡
የክልሉ መንገስት በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፤ የትግራይ ህዝብ ድምጽ ባልተወከለበት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የተላለፈው ውሳኔ “ህገ መንግስቱን እና የፕሪቶሪያን ስምምነት በግልጽ የሚጥስ ነው” ብሏል፡፡
ውሳኔው ግጭት አባባሽ እና ቀስቃስ ነው ያለው የክልሉ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔውን እንዲያስተካክልም ጠይቋል፡፡
ለብቻቸው በቀጥታ ምርጫ እንዲካሔድባቸው ውሳኔ ተላለፈባቸው አምስቱ የምርጫ ክልሎች፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለቀጣዩ ምርጫ በትግራይ ክልል ስር ዘርዝሯቸው የነበሩ የምርጫ ክልሎች ናቸው።
የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ባለፈው የካቲት 5 ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት በሁለቱ ክልሎች አወዛጋቢ በሆኑ ቦታዎች ላይ ስላሉ የምርጫ ክልሎች እና ጣቢያዎች ለቀረበላቸው ጥያቄ ቦርዱ የምርጫ ክልሎች እና ጣቢያዎቹን ዝርዝር ያወጣው “ከዚህ ቀደም ሲጠቀምበት በነበረበት ዝርዝር” መሰረት መሆኑን መናገራቸው ታወሳል።
“በቦርዱ የወጣው የምርጫ ክልል እና የምርጫ ጣቢያ አደረጃጀት በስድስተኛውም በአምስተኛውም ሀገራዊ ምርጫ ሲጠቀምባቸው የነበሩ ናቸው፤ የቀጣዩ ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ክልል እና ጣቢያዎችም በዚህ መነሻ ይፋ የተደረጉ መረጃዎችን ነው ያወጣነው” ማለታቸውም አይዘነጋም፡፡
የድምጽ መስጫ ቀኑ የፊታችን ግንቦት 24 እንደሚካሄድ ቀን የተቆረጠለት ሰባተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ዝግጅት እንደቀጠለ ሲሆን በዚህ ምርጫ ላይ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመወዳደሪያ ምልክቶቻቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡
ቦርዱ ለፖለቲካ ፓርቲዎች እና የግል ተወዳዳሪዎች ያወጣው የእጩዎች ምዝገባ ያወጣው የአንድ ወር ጊዜ ገደብ ዛሬ ተጠናቋል፡፡
ከ45 ሚሊዮን በላይ መራጮች የሚሳተፉበት የኢትዮያ ጠቅላላ ምርጫ ዝግጅት በመካሄድ ላይ ሲሆን ተወዳዳሪ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን የቀጠሉ ሲሆን የመራጮች ምዝገባም በሚቀጥለው ሳምንት ይጀመራል ተብሏል፡፡