በካናዳ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አማካኝነት የወጣው ይህ ማስጠንቀቂያ ‹‹ወሳኝ ላልሆነ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ወደ ኢትዮጵያ እንዳትሄዱ› የሚል መልእክት ያለው ሲሆን ለዚህም የሰጠው ምክንያት የእርስ በእርስ ግጭት፣ አመፅ፣ የጦር መሳሪያ ግጭት ወንጀል እና የማርበርግ ቫይረስ ስርጭት ናቸው።
የጉዞ ማስጠንቀቂያው የፀጥታ ሁኔታው ድንገት ሊባባስ እንደሚችል አሳስቦም ይህ ማስጠንቀቂያ አዲስ አበባን እንደማይመለከት አስታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ ዜጎቹም ቢሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ገልፆ በከተማው ውስጥ የወንጀል መጠኑ ከፍተኛ መሆኑንና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች እየተካሄደ ያለው የትጥቅ ትግል ያለምንም ማስጠንቀቂያ ወደ ከተማው ሊዛመት የሚችልበት እድል እንዳለ አስታውቋል፡፡
ይህ ማስጠንቀቂያ እንዳለው የካናዳ ዜጎች ከአዲስ አበባ ውጪ ወደ አማራ፣ ትግራይና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ፈፅሞ መጓዝ የለባቸውም ብሏል፡፡
እንዲሁም ወደ ጋምቤላና ሲዳማ በኦሮሚያ ክልል ደግሞ ሰሜን ሸዋ፣ ምእራብ ሸዋ፣ ምእራብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋና ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞኖች ፈፅሞ መሄድ እንደሌለባቸው በማስጠንቀቂያ መልዕክቱ ላይ ተጠቅሷል።
ካናዳዊያን የጉዞ ማስጠንቀቂያውን ችላ ብለው ወደ ተጠቀሱት ቦታዎች ከሄዱ በእርስ በእርስ ግጭት መሀል ሊገቡ እንደሚችሉ ወይንም ሊታገቱ እንደሚችሉና የአውሮፕላን ጥቃት ሰለባም የመሆን እድል እንደሚያጋጥማቸው አሳስቧል።