ኢትዮጵያ የኤርትራ ፖሊሲዬ “ሙሉ በሙሉ ከሸፈ” አለች

ከኤርትራ ጋር በትብብር ላይ የተመሰረተ፣ አዎንታዊ እና ገንቢ የረጅም ጊዜ ግንኙነትን ለመመስረት የሚያስችል አካሄድን ወይም ፖሊሲን ስንከተል ነበር ያሉት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ፖሊሲው አሁን “ሙሉ በሙሉ ከሽፏል” ብለዋል።

ለፖሊሲው መክሸፍ “አጋጣሚውን መጠቀም አልተቻለም” ያሉትን የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን የኤርትራ አገዛዝ ተጠያቂ አድርገዋል።

አገዛዙ በኢትዮጵያ ላይ እየተከተለ ባለው ‘የተሳሳተ’ ፖሊሲ ምክንያት ዘላቂ ግንኙነት ለመመስረት የተደረጉ ሙከራዎች ሁሉ ሙሉ በሙሉ መክሸፋቸውንም ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ትኩረቱን በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና በአፍሪካ ቀንድ ዙሪያ ባሉ ወቅታዊ የፖለቲካና የደህንነት ሁነቶች ላይ
አድርጎ ትናንት ሐሙስ ህዳር 4 ቀን 2018 ዓ/ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ መኮንን አዳራሽ በተካሄደ የውይይት መድረክ ላይ የተናገሩት።

በመድረኩ ሁነቶችን በወጉ አስተንቶ የያዘ ጥናታዊ መልክ ያለው ወረቀትን ያቀረቡት ዶ/ር ጌዲዮን ለአንድ ሰዓት ያህል በዘለቀ ንግግራቸው በተለይ ከኤርትራ ጋር እየተፈጠረ ያለው መካረር መነሻዎች ምን እንደሆኑና የኢትዮጵያ አቋም ምን እንደሆነ ዘርዘር አድርገው አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ በተለይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሚመራው አዲሱ የለውጥ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ሻክሮ የቆየውን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በማስተካከልና ቁርሾዎችን በማስቀረት ግንኙነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከማድረግም በላይ ዲፕሎማሲያዊ መገለል ውስጥ የነበረችው ኤርትራ ዳግም ወደ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንድትመለስና ማዕቀቦች እንዲነሱላት ለማድረግ የሚያስችሉ ዲፕሎማሲያዊ ተግባራትን ሲያከናውን ስለመቆየቱ ገልጸዋል።

ሆኖም ወትሮም ቢሆን “ንቀትና ጥላቻ” በውስጡ ላደረው ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አገዛዝ ይህ እንዳልተዋጠ ነው የተናገሩት ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ውጥረት መፍጠሩንና መካረር ውስጥ መግባታቸውን በመጠቆም።

ከኤርትራ ነጻነት በፊትና በኋላም ይኸው የተካረረ ፖለቲካዊ ሁኔታ ገዢ ፖሊሲ ሆኖ ስለመቀጠሉ ያነሱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ
አሁናዊው መካረር ከኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ፍላጎት ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ የሚያሳይም ነው ብለዋል የኢሳያስ አገዛዝ ስለ ባህር በር ጉዳይ አንተስተው ለማያውቁ የቀደሙ የኢትዮጵያ መንግስታት ጭምር ከባድ ጥላቻ እንደነበረው በማከል።

ለዚህ የቀድሞ የትግል አጋራቸው ህወሓት ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት በ1990ዎቹ መባቻ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረገውን ከባድ ደም አፋሳሽ ጦርነት በማሳያነት አንስተዋል።

አገዛዙ ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ እንኳን ሳይቀር ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ ለማድረግ አልሸባብን መሰል አሸባሪ ቡድኖችን እስከመደገፍ ደርሶ ነበርም ብለዋል የደም አፋሳሹ ጦርነት “በድንበር ጉዳይ የመጣ ነው” በሚል የሚሰጡ ትንተናዎች የተሳሳቱና “ግልብ” እንደሆኑ እንዲሁም ጉዳዩ ጥልቅ መረዳትን እንደሚፈልግ በመጥቀስ።

ዶ/ር ጌዲዮን አሁናዊ የሁለቱ ሀገራት ውጥረትም ቢሆን ከዚሁ ከአገዛዙ ባህሪ እንደሚመነጭ በማሳትም ዋና ናቸው ያሏቸውን አምስት ቁልፍ ጉዳዮች ጠቅሰው አብራርተዋል።

አገዛዙ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ደጋግሞ ለመግባትና በኢትዮጵያ መቃብር ላይ ነጻና ሉዓላዊት ኤርትራን ለመገንባት ከመመኘት ባሻገር ታጣቂዎችን ማሰልጠንና ማስታጠቁ፣ ለኢትዮጵያ በጎ ለማይመኙና ሌሎች ቀጣናዊ ፍላጎት ላላቸው የውጭ ኃይሎች መሳሪያ ሆኖ ማገልገሉ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ማክበዱን፣ ያልተጻፈው ነገር ግን ከዕለት ወደ ዕለት ይበልጥ እያደገ የመጣውና በቀል የተጫነው “ኤርትራ እንደ ሀገር ልትቀጥል የምትችለው ኢትዮጵያ ስትዳከምና መረጋጋት ሳትችል ስትቀር ነው” የሚለው የኢሳያስ ቀኖናዊ እሳቤ ( the Isaias Doctrine)፣ አገዛዙ የሀገሪቱንም ሆነ የዜጎቿን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የሰራው ነገር አለመኖሩና ይህም የፈጠረበት ከባድ ስጋት፣ ቁንጮ የአገዛዙ ባለስልጣናትና መሪዎች ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ከዘለቀው ጦረኛ እሳቤያቸው እስካሁን ድረስ መላቀቅ አለመቻላቸው (the Nakfa Syndrome) የሰመረ ግንኙነት ለመመስረት የነበሩ ፍላጎቶችን አዳጋች እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።

የኤርትራ መገንጠልና ሀገር የመሆን ጉዳይ በወቅቱ ያን የማድረግ ስልጣን ባልነበረው የሽግግር መንግስት ከመፈጸሙም በላይ ኢትዮጵያ ያለ ባህር በር እንድትቀር ስለተደረገበት ኢፍትሐዊ መንገድ ያነሱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አሁንም ቁጥሩ በየጊዜው የሚጨምር ህዝብና የሚያድግ ኢኮኖሚ ላላት ኢትዮጵያ የዘላቂና አስተማማኝ ባህር በር ጉዳይ “የህልውና ጉዳይ ነው” ብለዋል።

ሆኖም ይህ ለኤርትራው የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አገዛዝ የሚዋጥ አይደለም እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ።

በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚኖር መካረርና ውጥረት ወትሮውንም ቢሆን ሰላም የራቀውን የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን የበለጠ ከማተራመስ ባለፈ ለመላው ምስራቅ አፍሪካ እጅግ አደገኛና አውዳሚ ይሆናል ሲሉ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ እና በግዛታዊ አንድነቷ
ላይ ትንኮሳዎችና ጥሰቶች እየተፈጸሙ ራሷን ለመከላከል የሚያስችሉ አጸፋዊ እርምጃዎችን ከመውሰድ የተቆጠበችው በዚሁ ምክንያት እንደሆነም ነው ዶ/ር ጌዲዮን የተናገሩት።

የኤርትራ ወታደሮች አሁንም በሰሜን ኢትዮጵያ ጥቂት የማይባሉ አካባቢዎችን ተቆጣጥረው እንደሚገኙ ያስታወሱት የኤርትራ መንግስት አሁንም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት በመንግሥት ላይ ነፍጥ ያነሱ ታጣቂ ቡድኖችን እየደገፈ እንደሚገኝ በማንሳትም ይህ ብቻውን ለኢትዮጵያ ራሷን ለመከላከል የሚያስችል በቂ ምክንያት ቢሆንም አሁንም ታቅባ መቆየትን ምርጫ ስለማድጓ ገልጸዋል፤ ሆኖም ትንኮሳውን ከዚህ በላይ መሸከሙ ሊከብድ እንደሚችል በመጠቆም።

በመሆኑም “አንድ ህዝብ” ያሏቸው ሁለቱ ሀገራት በመካከላቸው የተፈጠረውን የተካረረ ቅራኔ ምጣኔ ሀብታዊ ውህደትን ጨምሮ በሌሎችም ዘርፎች ሊደረጉ በሚችሉ የሁለትዮሽና ቀጣናዊ ትብብሮች ሊፈቱ እንደሚችሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ለዚህ ግን የቀጣናው ሀገራት ከብሔራዊ ጥቅማቸው የተጣጣመ ስትራቴጂ ሊኖራቸውና ቀጣናውን አዳክመው ሊበዘብዙት ለሚፈልጉ ከቀጣናው ውጭ የሆኑ ሀገራት መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ሊጠነቀቁ እንደሚገባ አሳስበዋል። ሆኖም ከቀጣናው ውጭ ያሏቸው ሀገራት እነማን እንደሆኑ በግልጽ አልጠቀሱም።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም የኤርትራ መንግስት በተደጋጋሚ ከሚያደርገው ከእንዲህ ዐይነቱ ጸብ አጫሪ ድርጊቱና ትንኮሳዎቹ ይታቀብ ዘንድ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን በማድረግ የበኩሉን ሚና እንዲጫወትም ጥሪ አቅርበዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *