የአፍሪካ ኢንሹራንስ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ

57 በመቶ የሚሆኑት የአፍሪካ ሀገራት ለከፍተኛ የእዳ ችግር መጋለጣቸው ተገልጿል።

እነዚሁ ታዳጊ ሀገራት በተያዘው ዓመት ብቻ ከ 80 ቢሊዮን ዶላር በላይ የዉጪ እዳ እንዲከፍሉ ይጠበቃል

በአፍሪካ የሕዝብ ዕዳ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የአፍሪካ ኢንሹራንስ ድርጅት አስታውቋል ።

እንደ ድርጅቱ መረጃ ከሆነ በአህጉሪቱ ከሚገኙ ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት መካከል 57% የሚሆኑት በዕዳ ችግር ውስጥ ገብተዋል ወይም ከፍተኛ የዕዳ ስጋት ላይ ይገኛሉ።

ይህንን አኃዝ የገለጹት የድርጅቱ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ፓቲ ማርቲን በአዳስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘዉ 51ኛዉ የአፍሪካ ኢንሹራንስ ድርጅት ዓመታዊ ኮንፍረንስ እና ጠቅላላ ጉባኤ መድረክ ላይ ሲሆን :- በዚህ ንግግራቸው የዕዳው ጫና መጨመር ዋና ዋና መንስኤዎች የዓለም አቀፍ የገበያ መዋዠቅ እና የሸቀጦች ዋጋ መለዋወጥ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

እ.ኤ.አ. ማርች 11፣ 2025 በ One Data Analysis በተዘመነው መረጃ መሠረት፣ የብዙ የአፍሪካ ሀገራት የፋይናንስ ሁኔታ እጅግ ደካማ ነው። ከ2023 ጀምሮ የአፍሪካ ሀገራት ለውጭ አበዳሪዎች በድምሩ 685.5 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ አለባቸው ተብሎ ይገመታል።

ለዕዳ አገልግሎት የሚከፈለው ክፍያም እንዲሁ አሳሳቢ ሲሆን፣ ትንበያዎች እንደሚያመለክቱት የአፍሪካ ሀገራት በ2025 ብቻ 88.7 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ዕዳ አገልግሎት እንዲከፍሉ ይጠበቃል።

ይህ የውጭ ዕዳ ጫና በ2023 ከአፍሪካ ሀገራት አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) 24.5% ጋር እኩል መሆኑ የችግሩን ስፋት ያሳያል።

ወ/ሮ ፓቲ የሕዝብ ዕዳ ለመንግስታት የልማት ወሳኝ መሳሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል፣ ወጪዎችን ለመሸፈን፣ ሕዝባቸውን ለመጠበቅ እና ለተሻለ የወደፊት ሕይወት ኢንቨስት ለማድረግ እንደሚረዳ ቢገልጹም፣ አሁን ያሉት አኃዛዊ መረጃዎች ግን አሳዛኝ ሁኔታን የሚያሳዩ መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋትን ለመከላከል በአህጉሪቱ ጠንካራና ዘላቂነት ያለው የዕዳ አያያዝ ስልቶች በአስቸኳይ እንደሚያስፈልጉ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የብድር ጫና ካለባቸው ሀገራት መካከል ስትሆን ከ60 ቢሊዮን ዶላር በላይ እዳ እንዳለባት ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማህበር አስታውቋል።

ማኅበሩ እንደገለጸው እስከ አውሮፓዊያኑ 2023 ድረስ የኢትዮጵያ የብድር መጠን 62 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል ብሏል።

ይህን ተከትሎም የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የዕዳ ድርሻ ወደ 575 ነጥብ 6 ዶላር ማሻቀቡንም ማህበሩ በሪፖርቱ ላይ ገልጧል።

የአገሪቱ የብድር ጫና በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር አስተዋጽዖ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል፣ የመንግሥት የወጪ አስተዳደር አቅም ማነስ፣ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ደካማነት፣ ኢኮኖሚውን ሊደግፉ የሚችሉ ፕሮጀክቶች አለመስፋት፣ የወጪ ንግድ መቀዛቀዝና የማምረት አቅም እየቀነሰ መሄዱ እንደሚገኙበት የተቋሙ ሪፖርት ጠቅሷል፡፡

ከፍተኛ የብድር ጫና ካለባቸው የአፍሪካ ሀገራት መካከል ግብጽ፣ ኬንያ፣ አንጎላ፣ ኮትዲቯርና ደቡብ አፍሪካ ዋነኞቹ ናቸው።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *