በትግራይ ዜጎች ዳግመኛ ግጭት ይቀሰቀሳል በሚል ስጋት ባለፉት ሶስት ቀናት ዉስጥ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ሸመታ ላይ ናቸዉ ተብሏል፡፡
በዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው የህወሓት ክንፍ የተሾሙ የተባሉ ግለሰብ በሚሊሻዎች ታጅበው ትናንት የመቐለ 104 ነጥብ 4 ኤፍኤም ሬድዮ ጣብያ ለመቆጣጠር መሞከራቸው ተከትሎ በሬድዮ ጣብያው ውዝግብ ተፈጥሮ ነበር።
ታጣቂዎቹ ከዚህ ቀደም በትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር የተሾሙትን የጣቢያው ሃላፊ አውርደው በሌላ ሰው የመተካት እንቅስቃሴ ማድረጋቸውንና የከተማዋ ፖሊስ ደርሶ ድርጊቱን ማስቆሙ ታውቋል።
የወታደራዊ አመራሮቹ ውሳኔ ተከትሎ ደግሞ ግጭት እንዳይነሳ የሰጉ የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች ገንዘባቸው ከባንክ ማውጣት እና ሸቀጦች መግዛት ላይ ተጠምደዋል መባሉን ዶቼ ቬለ ዘግቧል።
ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመቐለ ዲስትሪክት ሰራተኞች እንደሰማነው ከወታደራዊ አመራሮቹ ውሳኔ በኃላ በነበሩ ሶስት ቀናት ብቻ ከግማሽ ቢልዮን በላይ ብር ከባንኩ ቅርንጫፎች በደንበኞች ወጪ ተደርጓል።
በገበያዎች በተለይም የምግብ ነክ ሸቀጦች የሚገዛ በዝቷል፣ የተወሰነ የዋጋ ጭማሪም ይስተዋላል ተብሏል። በሌላ በኩል በበርካታ ነዳጅ ማደያዎች በተለይም ቤንዚን የሌለ ሲሆን በጥቁር ገበያ አንድ ሊትር ከ270 እስከ 300 ብር ይሸጣል።
ይህንኑ ተከትሎም በመቀሌ እና በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች የትራንስፖርት ዋጋ እንደተወደደ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ከአራት ዓመት በፊት የትግራይ ታጣቂዎች በመቀሌ በሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መክፈታቸውን ተከትሎ ለሁለት ዓመት የዘለቀ ጦርነት ሲካሄድ ነበር፡፡
ይህ ጦርነት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተካሄደ የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ቆሟል፡፡
ስምምነቱን ተከትሎ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳድር የተመሰረተ ሲሆን በህወሃት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል እና በወቅቱ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳድር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ መካከል የስልጣን ፉክክር ተከስቷል፡፡
የሁለቱን ፉክክር ተከትሎ በትግራይ ክልል የፖለቲካ አለመረጋጋት የተከሰተ ሲሆን በክልሉ ዳግም ጦርነት እንዳይከሰት ከፍተኛ ስጋት አንጃቧል፡፡