የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸሙን ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡
ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ለሚኒስትሩ ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል በኢትዮጵያ የኤልክትሪክ መኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች ቁጥራቸው እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ የመለዋወጫ አካላት ፍላጎትን እንዴት ሊሸፈን ታስቧል? የሚለው ዋነኛው ነበር፡፡
ከኤሌክትሪክ መኪና ውስጥ የባትሪ ጉዳይ ዋናው በመሆኑ ወደ ፊት ለባትሪ የሚወጣው ውጪ ምንዛሪ ፈታኝ እንዳይሆን በሃገር ውስጥ ለማምረት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ምን እየሰራ ነው ሲሉም የምክር ቤቱ አባላት ጠይቀዋል፡፡
አቶ መላኩ በምላሻቸው የኤሌክትሪክ መኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች በክልሎችም ጭምር እየጨመረ መምጣቱን መልካም ነው ምክንያቱም ሃገሪቱ በየአመቱ ለነዳጅ የምታወጣውን 4 ቢልዮን ዶላር ያስቀራል ብለዋል፡፡
የኤሌክትሪክ መኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች እየበረከቱ ቢመጡም የባትሪው ጉዳይ ግን ሊታሰብበት እንደሚገባም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
የኤሌክትሪክ መኪኖች የተወሰነ ዓመታት ካገለገሉ በኋላ ባትሪያቸው እየደከመ ይመጣል ያሉት አቶ መላኩ አሁን ባለው አለማቀፍ ገበያ ደግሞ የአንድ ኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ ከ5,000 እስከ 10,000 ዶላር ነው ይህም ወደ ኢትዮጵያ ብር ሲመነዘር ከ500 ሺህ ብር በላይ ይጠጋል ስለዚህ በሃገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ባትሪ ማምረቻ ማቋቋም ወሳኝ ሆኖ ይታያል ብለዋል፡፡
እንደ አጋጣሚ እና መታደል ሆኖ ኢትዮጵያ ለባትሪ ማምረት የሚረዳ ሊትየም እና ሌሎች ማዕድኖች አሏት ይህንን ተጠቅመን በሃገር ውስጥ ባትሪ ለማምረት ከሚመለከታቸው እና በዚህ ዘርፍ ላይ ለማምረት አቅም ካላቸው ጋር ውይይት እያደረግን ነው ሲሉም አቶ መላኩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ካሏት ማዕድናት መካከል ሊቲየም እና ታንታለም ማዕድናት ያሏት ሲሆን በተለይም በኦሮሚያ ክልል ያለው በቀንቲቻ ማዕድን ማውጫ ስር ገኛ፡፡
በዚህ ቦታ 110 ሚሊዮን ቶን ሊቲየም ማዕድን እንዳላት ከዓመታት በፊት ይፋ የተደረገው የኢትዮጵያ ማዕድናት ጥናት ሪፖርት ያስረዳል፡፡
ኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በፊት በነዳጅ የሚሰሩ መኪኖች ወደ ሀገሯ እንዳይገቡ እገዳ ጣለች ሲሆን መኪና አስመጪዎች የኤሌክትሪክ መኪኖችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ላይ ናቸው፡፡
ይሁንና ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ የኤሌክትሪክ መኪኖች የመለዋወጫ እጥረት፣ የጥገና ባለሙያ፣ ሀይል መሙያ ማዕከላት እና ሌሎች አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማት አልተሟሉም፡፡
በዓመት ለነዳጅ ግዢ ከአራት ቢሊዮን ዶላር ወጪ የምታደርገው ኢትዮጵያ ይህን ወጪ ለመቀነስ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ትገኛለች፡፡
ለአብነትም በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መኪኖች ብቻ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መፍቀድ፣ የነዳጅ ድጎማዎችን ቀስ በቀስ ማንሳት፣ አሮጌ እና ረጅም ዓመታት አገልግሎት የሰጡ መኪኖችን ማገድ እና ሌሎችም እርምጃዎችን እየወሰደች ትገኛለች፡፡
በኢትዮጵያ ከ400 በላይ ተቋማት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ እያስመጡና እየገጣጠሙ ነው የተባለ ሲሆን ሁሉም አስመጪዎች እና ገጣጣሚዎች የኃይል መሙያ እንዳላቸውም ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ከአንድ ሳምንት በፊት ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሃይል መሙያ ማሽን (ቻርጀር) መትከል የሚፈቅድ መመሪያ ማዘጋጀቷ ይታወሳል።
በዚህ መመሪያ መሰረትም በመንገዶች ግራና ቀኝ በየ50 ኪሎሜትር ልዩነት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን መሙላት የሚችል ፈጣን ቻርጀር ጣቢያ ማቋቋም ይፈቅዳል፡፡
ይሁንና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሃይል ማቅረብ የሚፈልጉ ተቋማት ከነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን ፈቃድ በመውሰድ እንዳለባቸው በመመሪያው ላይ ተጠቅሷል።
በተለያዩ ተቋማት የሚተከሉ የኤሌክትሪክ ሃይል መሙያዎች ከባለስልጣኑ ፈቃድ ማግኘት እንደሚጠበቅባቸውም ይደነግጋል፡፡