የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ “የክሪፕቶ አሴትን” እና የዲጂታል ገንዘብን በኢትዮጵያ መጠቀም የሚያስችል መመሪያ በቀጣይ ሊያወጣ እንደሚችል ገልጿል፡፡
የተቋሙ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ እንደገለጹት ብሔራዊ ባንክ የክሪፕቶ ከረንሲ መመሪያውን የሚያወጣው በማዕከላዊ ባንኪንግ፣ በገንዘብ ፖሊሲ እና በገንዘብ አስተዳደር ያሉ ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን እያየ መሆኑን ተናግረዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከ16 ዓመት በፊት የወጣውን እና በስራ ላይ ያለውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅን አጽድቋል፡፡
በምክር ቤቱ ተገኝተው ከፓርላማ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት አቶ ማሞ አዲሱ አዋጅ ካካተታቸው አዳዲስ ድንጋጌዎች መካከል ክሪፕቶ ከረንሲ እና የዲጂታል ገንዘብን መጠቀም የተመለከቱት ይገኙበታል፡፡
የጸደቀው አዋጅ “አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ብሔራዊ ባንክ ካልፈቀደ በስተቀር፤ ክሪፕቶ ከረንሲ ወይም ሌላ ማንኛውንም ዲጂታል ወይም የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ በመጠቀም ክፍያ መፈጸም አይችልም” ሲል ይከለክላል።
አዋጁን በመተላለፍ በእነዚህ መንገዶች ክፍያ የፈጸመ ማንኛውም ሰው፤ ከሶስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት እና ከአስር ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ እንደሚቀጣም ይደነግጋል።
በኢትዮጵያ የክሪፕቶ ማይኒንግ በዚህ ደረጃ ላይ ቢገኝም፤ “የክሪፕቶ አሴትን” እንደ ገንዘብ መጠቀም በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ የተፈቀደ አለመሆኑን አቶ ማሞ ገልጸዋል።
ይሁንና በቀጣይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት የክሪፕቶከረንሲ ግብይቶች የሚመሩበት መመሪያ ሊያወጣ እንደሚችል አቶ ማሞ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በዲጂታል መረጃ ማቀነባበር ለተሠማሩ የውጭ ኩባንያዎች ከተሸጠ ኤሌክትሪክ ኃይል ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል መናገሩ ይታወሳል።
ካሳለፍነው ዓመት ጀምሮ በኢትዮጵያ የቢትኮይን ግብይት መፈጸም የሚያስችሉ መሰረተ ልማት ግንባታ የሚያደርጉ ኩባያዎች ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል፡፡
ኢትዮጵያ አሁንም የክሪፕቶከረንሲ ግብይት እንዲደረግ ያልፈቀደች ሲሆን የዳታ ማዕከል ግንባታዎች እንዲካሄዱ ግን ስምምነቶችን በመፈራረም ላይ ነች፡፡
መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የዎልስትሪቱ ቢትፉፉ የተሰኘው የክሪፕቶከረንሲ ኩባንያ በኢትዮጵያ መሰማራት የሚያስችለውን ሂደት መጀመሩን አስታውቋል፡፡
ኩባንያው የክሪፕቶከረንሲ ግብይት ማካሄድ የሚያስችል የ80 ሜጋዋት ኤሌክትሪክ ሀይል መሰረት ልማት መግዛቱን ገልጿል፡፡
ከሰባት ወራት በፊት ዌስት ዳታ ማዕከል የተሰኘው ኩባንያ የ250 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት በአዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ጋር ተፈራርሟል፡፡
በዚህ ስምምነት መሰረት የቢትኮይን ግብይት እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ጉዳዮች ዙሪያ ስልጠና መስጠት የሚያስችሉ እንደሆኑም ተገልጿል፡፡
የሩሲያ እና ቻይና ክሪፕቶከረንሲ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የዳታ ማዕከላቸውን ለመክፈት ፍላጎታቸው ከፍተኛ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ኢትዮጵያ ባዘጋጀችው የአይሲቲ ፓርክ ውስጥ የዳታ ማዕከላትን ለመገንባት ስምምነቶችን እየተፈራረሙ ናቸው፡፡
በዚህም መሰረት እስካሁን 25 የዳታ ማይኒንግ ድርጅቶች የተመዘገቡ ሲሆን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ጋር የሀይል አቅርቦት ስምምነትን ተፈራርመዋል ተብሏል።