ኢትዮጵያ 10 የኢንዱስትሪ ፓርኮቿን ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞንነት አሳደገች

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስፈላጊዉን መስፈርት አሟልተዋል ያላቸዉን 10 ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን እንዲያድጉ መወሰኑ ተገልጿል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በበኩሉ እንዳስታወቀው በስሩ ከሚያስተዳድራቸው 13 ኢንዱስትሪ ፓርኮችና የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና መካከል 10ሩ ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ማደጋቸውን አሳዉቋል።

አሁን በስራ ላይ ካሉ 13 ኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ያደጉት አዳማ ባህርዳር ፣ ቦሌ ለሚ ፣ ደብረ ብረሃን እና ሀዋሳ ፣ ጅማ ፣ ቂሊንጦ ፣ ኮምቦልቻ ፣ መቀሌ እና ሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ መሆናቸው ታዉቋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ለማሳደግ አዋጅ ቁጥር 1322/2016 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል።

ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞንነት ማደጋቸው የግል ዘርፉ በኢኮኖሚ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ እንዲሳተፉ ለማበረታታት፣ የሀገሪቱን የውጪ ባለሀብት ቀጥታ ኢንቨስትመንት የመሳብ እንቅስቃሴ ለማጠናከር፣የኢኮኖሚ ክላስተሮችን ለማስተዋወቅ እንደሚረዳ ታምኖበታል።

ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን እና የውጪ ንግድን ለማሳደግ በሚል ነበር ኢንዱስትሪ ፓርኮችን የገነባችው፡፡

አሁን ላይ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ያሏት ኢትዮጵያ ፓርኮች የምርታቸውን 50 በመቶ ለሀገር ውስጥ ገበያ እንዲያቀርቡ ፈቅዳለች፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰሩ ኩባንያዎች 50 በመቶ ምርታቸውን ለሀገር ውስጥ ገበያ እንዲያቀርቡ መፈቀዱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታውቋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰሩ ኩባንያዎች ምርታቸውን ሙሉ በሙሉ ለውጭ ገበያ እንጂ ለሀገር ውስጥ ማቅረብ ሳይፈቀድላቸው መቆየቱን የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን ገልጸዋል።

ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ተጽዕኖ ሥር የነበሩ ባለሃብቶችን ለማበረታታት በፓርኮች ውስጥ የሚሰሩ ኩባንያዎች 50 በመቶ ምርታቸውን ለሀገር ውስጥ ገበያ እንዲያቀርቡ በአዋጅ መፈቀዱን አስታውቀዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ አሜሪካ የተለያዩ የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን መጣሏ ይታወሳል፡፡

ከማዕቀቦቹ ውስጥ ኢትዮጵያን ከአሜሪካ ነጻ የንግድ እድል ወይም አግዋ ማገድ አንዱ ሲሆን በዚህም ምክንያት በተለይም የኢንዱስሪ ፓርኮች በማዕቀቡ ተጎድተዋል፡፡

ምርቶቻቸውን ወደ አሜሪካ፣ አውሮፓ እና እስያ ገበያዎች ይልኩ የነበሩ ኩባንያዎች አሜሪካ ማዕቀቧን ለተጨማሪ አንድ ዓመት በማራዘሟ ወደ ሌላ ሀገር እንዲሰደዱ እያደረገ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የእግዱ ዋነኛ ምክንያትም በጦርነቱ ምክንያት በዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ ነው የሚል ሲሆን ኢትዮጵያ የአሜሪካንን ውሳኔ ተቃውማም ነበር።

የአግዋ እድል መሰረዝ በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ባሉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የተቀጠሩ ዜጎችን ስራ አጥ በማድረግ በጦርነቱ ምንም አይነት ተሳትፎ የሌላቸው ኢትዮጵያዊያንን ይጎዳል ስትል ኢትዮጵያ አሜሪካ ውሳኔዋን እንድታጤነው ጠይቃም ነበር።

በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የተሰማሩ አብዛኞቹ የውጭ ሀገራት ኩባንያዎች ዋነኛ የገበያ መዳረሻዎቻቸው አሜሪካ ስትሆን በአግዋ እገዳ ምክንያትም የገበያ እጥረት እንዳጋጠማቸው ተናግረዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *