ኢትዮጵያ 251 ሚሊዮን ዶላር ብድር ከአይኤምኤፍ አገኘች

ዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይኤምኤፍ ለኢትዮጵያ 251 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ብድር እንደሚለቅ አስታውቋል፡፡

ተቋሙ እንዳስታወቀው ብድሩን ለመልቀቅ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ከስምምነት ላይ ደርሷል።

ድርጅቱ ብድሩን ለማጽደቅ የተስማማው፣ የድርጅቱ የባለሙያዎች ቡድን ከኅዳር 3 እስከ 17 በአዲስ አበባ ተገኝቶ ኹለተኛውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ግምገማ ማድረጉን ተከትሎ ነው።

የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ፣ የብድር መልቀቅ ስምምነቱን በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ እንደሚያጸድቀውና ወደፊት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ግምገማዎች በየስድስት ወሩ እንደሚካሄዱ ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።

የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንደተቀረፈና በመደበኛውና በትይዩ የውጭ ሀገራት መገበያያ ምንዛሬዎች መካከል ያለው ልዩነት ከ10 በመቶ በታች መውረዱን የጠቀሰው ድርጅቱ፣ መንግሥት ጥብቅ የገንዘብና ፊስካል ፖሊስ እንዲቀጥል አሳስቧል።

ኢትዮጵያ ካሳለፍነው ሐምሌ ወር ጀምሮ በአይኤምኤፍ እና ዓለም ባንክ ምክር ሀሳብ መሰረት የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲመራ ማድረጓ ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ የውጭ ንግድን ለማበረታታት በሚል ካሳለፍነው ሀምሌ ወር ጀምሮ የውጭ ምንዛሬ ግብይትን በገበያ እንዲመራ ውሳኔ ያስተላለፈች ሲሆን የብር የመግዛት አቅም ከእጥፍ በላይ ቀንሷል፡፡

አሁን ላይ አንድ የአሜሪካ ዶላር በአማካኝ በ124 ብር እየተመነዘረ ሲሆን በጥቁር ገበያ ደግሞ እስከ 140 ብር ድረስ እየተመነዘረ ይገኛል፡፡

የዓለም ባንክ የዳይሬክቶች ቦርድ ከአራት ወራት በፊት በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ውስጥ ለኢትዮጵያ የ16 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ብድር እና እርዳታ እንደሚሰጥ መግለጹ ይታወሳል፡፡

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ካጸደቀው ገንዘብ ውስጥ 1 ቢሊዮን ዶላር ቀጥተኛ ድጋፍ መሆኑን የገለጸው ባንኩ፤ 500 ሚሊዮን ዶላሩ ደግሞ የተራዘመ ብድር ነው ብሏል።

የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ እያከናወነችው ያለችውን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለመደገፍ በርካታ የድጋፍ ማዕቀፎችንም ይፋ አድርጓል።

በዚህም መሰረት 1 ቢሊዮን ዶላር የቀጥታ እርዳታ ሲሆን 500 ሚሊዮን ዶላር የእዳ ክፍያ ማራዘሚያ እንዲሁም 320 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ትብብር በሚል ለኢትዮጵያ የሚደረግ ድጋፍ ነው ተብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም 1 ነጥብ 15 ቢሊዮን ዶላር የባለብዙ ወገን ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ እንዲሁም 6 ቢሊዮን ዶላር ደግሞ በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ለበጀት ድጎማ እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡

2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ትብብር ለኢንቨስትመንት የምታገኘውን ሲጨምር ኢትዮጵያ አሁን ከምታገኘው 7 ቢሊዮን ዶላር በተጨማሪ በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት በጠቅላላው 16̂ ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር እንደምታገኝ ተገልጿል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *